“ሙስሊሙ ማኅበረሰብ የዒድ አል-አድሃ (አረፋ) በዓልን ሲያከብር በዞኑ የሚገኙ ተፈናቃይ ወገኖችን በመርዳት ሊኾን ይገባል” የሰሜን ጎንደር ዞን እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት

64

ደባርቅ: ሰኔ 21/2015 ዓ.ም (አሚኮ) 1ሺህ 444ኛው የዒድ ዓል-አድሃ (አረፋ) በዓል በሰሜን ጎንደር ዞን ደባርቅ ከተማ የእምነቱ ተከታዮች በተገኙበት እየተከበረ ይገኛል። በበዓሉ የተገኙት የሰሜን ጎንደር ዞን እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሼህ ከድር ዳውድ የዒድ ዓል-አድሃ (አረፋ) በዓል የመስዋዕትነት በዓል በመኾኑ በእምነቱ ተከታዮች ዘንድ ትልቅ ቦታ ይሰጠዋል ነው ያሉት።

የእምነቱ ተከታዮች የአደባባይ በዓሉን በሶላትና ሌሎች መንፈሳዊ ክዋኔዎች ካከበሩ በኋላ በየቤቱ የዕርድ ሥነ ሥርዓት በመፈጸም በዓሉን እንደሚያከብሩት አመላክተዋል። ሙስሊሙ ማኅበረሰብ የበዓሉን ትርጉም ተገንዝቦ በዓሉን በየአካባቢው የተራቡ፣ የተጠሙ፣ የታረዙና ያዘኑ ወገኖችን በማብላት፣በማጠጣት፣በማልበስ፣ በማፅናናት፣ በመረዳዳት እና በመተሳሰብ እንዲያከብሩ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ሼህ ከድር በዞኑ በጦርነት የተፈናቀሉ በርካታ ወገኖች እንደሚገኙ አንስተው ሙስሊሙ ማኅበረሰብ እነዚህን ወገኖች በመርዳት በዓሉን ሊያከብር ይገባል ብለዋል።

የበዓሉ ታዳሚዎች በበኩላቸው በዓሉን ሃይማኖታዊ ሥርዓቱ በሚያዘው መሠረት በስግደት፣ በሶላትና በመንፈሳዊ ትምህርት እንዳከበሩት ተናግረዋል።

የአደባባይ በዓሉ ሲጠናቀቅ በየቤታቸው ዕርድ እንደሚፈጽሙ ገልጸው ሃይማኖት፣ ብሄር፣ ዘር፣ ቀለምና መሰል ልዩነቶች ሳይገድቧቸው ሰውነትን አስቀድመው ከጎረቤቶቻቸው ጋር በደስታ እንደሚያከብሩትም ገልጸዋል።

የበዓሉ ዓላማ መረዳዳት፣ መተሳሰብና መተዛዘን ነው ያሉት ምዕመናኑ ገንዘብ በማዋጣትና ከሚመገቡት በመቀነስ የተፈናቀሉና የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳት በዓሉን እንደሚያከብሩት ተናግረዋል።

ዘጋቢ፦ አድኖ ማርቆስ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የዒድ አል አድሃ (አረፋ) በዓልን ችግረኞችን በማሰብና በመርዳት እያከበርን ነው” የደብረ ታቦር ከተማ ሙስሊሞች
Next articleደብረታቦር ዩኒቨርስቲ ከክርስቲያን ሪሊፍ ጋር በመተባበር ከ16 ሺ በላይ መፅሐፍትን ለትምህርት ቤቶች ድጋፍ አደረገ።