
ደብረ ታቦር: ሰኔ 21/2015 ዓ.ም (አሚኮ) 1 ሺ 444ኛው የዒድ አል አደሃ (አረፋ) በዓል በደብረታቦር ከተማ በተለያዩ ሃይማኖታዊ ክዋኔዎች ተከብሯል፡፡
የዒድ አል አደሃ (አረፋ) በዓል ነብዩ ኢብራሒም ልጃቸውን ኢስማኤልን እንዲሰው ከፈጣሪያቸው ከአሏህ በታዘዙ ጊዜ በፍጹም ታዛዥነትና እምነት ለመሰዋት ሲዘጋጁ ፈጣሪያቸውም በልጃቸው ፈንታ የእርድ በግ ያቀረበላቸው የእምነት የታዛዥነትና የእዝነት በዓል ነው፡፡
ይህን እስላማዊ ታሪክና አስተምህሮም የደብረ ታቦር ከተማ ሙስሊም ማኅበረሰብ በእዝነት፣ በስግደት፣ በጸሎትና በትምህርት እያከበሩት ነው፡፡
የደብረታቦር ከተማ መስጊደል ኡስማን ኢማም ሼህ ሸፈቀው ሙሐመድ በዓሉ የመታዘዝና የእዝነት መኾኑን ጠቅሰው በበዓሉ ለችግረኞች በጀምዓው በግ በማቅረብ ለምስኪኖች ማከፋፈል የነፍስ ዋጋ እንዳለውና የእስልምና ትዕዛዝ እንደኾነ ተናግረዋል፡፡
የደብረታቦር ከተማ ቢላል መረዳጃ ማኅበር ኮሚቴ አባል ወርቁ ሰይድ በበዓሉ ችግረኞችም ተደስተው እንዲውሉ ድጋፍ መደረጉን ገልጸዋል፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ በበዓሉ ለችግረኞች የሚደረገውን ድጋፍ አሠራር በማሻሻል ቢላል የመረዳጃ ማኅበር ተመስርቶ ችግረኞች እንደችግራቸው ሁኔታ ድጋፍ እየተደረገላቸው ነው ብለዋል፡፡
ሕዝበ ሙስሊሙን በማስተባበርና በዓሉ ሃይማኖታዊ ሥርዓቱን ጠብቆ በሰላም እንዲከበር የከተማው ሙስሊም ወጣቶች ማገልገላቸውን የደብረታቦር አሊፍ ወጣቶች ጀምዓ ተወካይ ወጣት አህመድ ዉበቱ ተናግሯል፡፡
“የሙስሊምም ኾነ የክርስቲያን በዓል ሲከበር ከክርስቲያን ጓደኞቼ ጋር ተደስተን እናከብረዋለን” ያለው ወጣት አህመድ በዓሉን ከማክበር በተጨማሪ የእስልምና ዲን ሰላምን የሚያስተምር ስለኾነ ለሰላም በመጸለይና በመሥራት እናከብረዋለን ብሏል፡፡
በበዓሉ ላይ የተገኙት የደብረታቦር ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ወርቁ መርሻ እስልምና ለሰላም ያለውን ከፍተኛ አበርክቶ ጠቅሰዋል፡፡ የደብረታቦር ከተማ የመልካም አሥተዳደርና የመልማት ጥያቄዎችን እየመለሰ መኾኑንና ለዚህም የሙስሊሙ ማኅበረሰብ ድርሻ ከፍ ያለ መኾኑን ጠቅሰው ከተማ አሥተዳደሩ የደብረታቦር ከተማ ሙስሊም ኅብረተሰብ ጥያቄዎችን እንደሚፈታ ነው ኀላፊው የተናገሩት፡፡
ዘጋቢ፡- ዋሴ ባየ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!