
ባሕር ዳር: ሰኔ 21/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የመታዘዝ ተምሳሌት የኾነው ዒድ አል አድሃ (አረፋ) በመላው ዓለም የሚገኙ የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ በድምቀት ከሚያከብሩት በዓላት መካከል አንዱ ነው፡፡
አረፋ የተለያዩና የተራራቁ የሚገናኙበት፣ ዘመድ አዝማድ የሚሰባሰብበት፣ ጓደኛ፣ ጎረቤት የሚጠራራበትና የተነፋፈቀ ናፍቆቱን የሚወጣበት በዓል ነው፡፡
የበዓሉ ስያሜ በእስልምና ታሪክ ትልቅ ቦታ ከሚሰጠው ከአረፋ ተራራ ጋር የተሳሰረ ነው፡፡ እንደ ሃይማኖቱ አስተምህሮ የአረፋ በዓል መነሻው ተራርቀው እና ተጠፋፍተው ቆይተው የነበሩት አደም እና ሀዋ የተገናኙበት ነው፡፡
አደም እና ሀዋ ከነበሩበት የጀነት ዓለም ወጥተው ወደ ምድር ከመጡ በኋላ ለብዙ ዘመናት ሳይገናኙ ተራርቀው ቆይተዋል፡፡ በመለያየታቸውም ተነፋፍቀዋል፤ ከመነፋፈቅም አልፈው ተረሳስተዋል፡፡
ከተለያዩ ከረዥም ዘመን በኋላ ሲገናኙ መጀመሪያ፣ “ዐረፍተኒ” “አረፍቱከ” ነው የተባባሉት፡፡ ይህም፣ “አወቅሽኝ” “አወቅኩህ” ማለት ነው:: ከዚያም በኋላ የተገናኙበት ቦታ አረፋ ተባለ፡፡
በእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ ከነቢዩ ሙሐመድ (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) ቀጥሎ ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸው ነቢዩላህ ኢብራሂም (ዐለይሂ ሰላም) ከፈጣሪ የቀረበላቸውን ትልቅ ፈተና በድል የተወጡበት ዘመን ነበር፡፡ አንድ ቀን በህልማቸው ፈጣሪ በስተርጅና ያገኙትን ልጃቸውን እንዲሰውለት ሲጠይቃቸው ታያቸው፡፡ ፈጣሪያቸውን አብዝተው የሚወዱት ነቢዩ ኢብራሂም (ዐ.ሰ) ልባቸው ክፉኛ ቢያዝንም ልጃቸውን ለመሠዋት ወሰኑ፡፡
አባትና ልጅ የፈጣሪን ትዕዛዝ ለመፈጸም ከመካ ከተማ 20 ኪሎ ሜትር ርቆ ወደሚገኘው አረፋ ተራራ ሄዱ፡፡ ከተራራው አናት ላይ ነቢዩ ኢብራሂም (ዐ.ሰ) ልጃቸውን ለመሠዋት በተዘጋጁበት ቅጽበት “ኢብራሂም ታላቅነትህን አስመስክረሃልና እርዱን አቆየው” የሚል ድምጽ ከመልዕክተኛው ጅብሪል ሰሙ። በምትኩም መልዓኩ ከጀነት ያመጣውን በግ እንዲያርዱና ልጁን ወደ ቤቱ እንዲመልሱ ነገራቸው፡፡
አባት እና ልጅ ለፈጣሪ መታዘዝን በግልጽ ያሳዩባት ያቺ ዕለት የዒድ አል አድሀ በዓል ኾና እንድትከበርም ተወሰነ፡፡ እናም የአረፋ ተራራ ቦታው ለዒድ አል አድሀ በዓል መሠረት የኾነ በእስልምና ሃይማኖት ውስጥ ትልቅ ገድል የተሠራበት ነው፡፡
በአረፋ ወቅት ከሚከናወኑት ሃይማኖታዊ ተግባራት ውስጥ ዘር፣ ቀለም፣ ቋንቋ፣ ዜግነት፣ ፆታ፣ ዕድሜ፣ ሥልጣን፣ ሃብት ሳይለያቸው በአንድነት እና በእኩልነት የሚቆሙበት የሐጅ ሥርዓት ማከናወን እንዲሁም ኡድሂያ (ዕርድ) ማድረግ ናቸው፡፡
እርድ መፈጸም የአረፋ በዓል መገለጫ አንዱ ሲኾን እርዱ የሚከናወነውም በሃይማኖታዊ ትዕዛዙ መሠረት በመኾኑ ነው፡፡ በበዓሉ እርድ የሚፈጽም ሰው ከሥጋው አንድ ሦስተኛውን ለችግረኞች የመስጠት ኀላፊነት አለበት፡፡ ያለው ለሌለው ማካፈል እንደሚገባው፣ ከራስ አልፎ ለሌላው ደስታ እንደሚለግስ፣ እርስ በርስ መረዳዳትን፣ አንድነትን፣ መተሳሰብን እና መተዛዘንን የሚያበለጽግ ለመጭው ዓለም ብቻ ሳይኾን በምድራዊ ሕይወትም ደስታን የሚሰጥ መኾኑን ሃይማኖቱ ያስተምራል፡፡
በእመቤት አሕመድ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!