
ባሕር ዳር፡ ሕዳር 25/2012ዓ.ም (አብመድ) በዘንድሮው የጥምቀት በዓል በርካታ የውጭ ሀገራት አምባሳደሮችና ቱሪስቶች ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ከመላው ኢትዮጵያ የተውጣጣ የሽማግሌዎች ልዑክ ቡድንም በተለያዩ ክልሎች ከተንቀሳቀሰ በኋላ መዳረሻውን በጥምቀት በዓል ጎንደር እንደሚያደርግ ተነግሯል።
በጎንደር ከተማ በሚስተዋሉ ወቅታዊ ሁነቶች ዙሪያ በተካሄደው የምክክር መድረክ የጥምቀት በዓልን በጎንደር ከተማ ከምንግዜውም በተሻለ ድምቀትና መንገድ ለማክበር ሰፊ ርብርብ ሊደረግ እንደሚገባ ተነስቷል።
አቶ ሲሳይ አስማረ የጎንደር ሠላምና ልማት ሸንጎ አባል ናቸው፤ የጥምቀት በዓልን ለማክበር ሰፊ እንቅስቃሴ ያለ መሆኑን ተናረዋል፡፡ በርካታ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንም በበዓሉ ለመታደም እየተዘጋጁ ስለሆነ ሁሉም የከተማው ነዋሪና መንግሥት ሰፊ ቅድመ ዝግጅት እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።
የጎንደር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ማስተዋል ስዩም (ኢንጂነር) ደግሞ የከተማ አስተዳድሩ ዘንድሮ የጥምቀት በዓልን በድምቀት ለማክበር በርካታ እንግዶችን ከዓለም ዙሪያ የመጋበዝ ሥራ እየተሠራ መሆኑን ጠቅሰው ‹‹ከተማዋ ከነበረችበት የሠላም እጦት ሙሉ በሙሉ የወጣች መሆኑን የምናበስርበት ትልቅ አጋጣሚ ነው›› ብለዋል።
የከተማው ባሕል፣ ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ አስቻለው ወርቁ ለአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት በሰጡት መረጃ ደግሞ በቂ በጀት ከመመደብ ጀምሮ አስፈላጊው ሥራ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር እየተሠራ ነው፤ ጎንደርን ወደ ቀድሞ የሠላምና የጎብኝዎች መዳረሻነቷ ለመመለስም ጥረት እየተደረገ ነው።
ሕዝቡ የተለመደ የእንግዳ መቀበል ባሕሉን መሠረት አድርጎ ከወዲሁ ቅድመ ዝግጅት እንዲያደርግ አሳስበው በተለይም ከገበያ እና ንግድ አኳያ ተገቢ እንቅስቃሴ እንዲኖር እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል።
የአማራ ክልል ሠላምና ደኅንነት ግንባታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አገኘሁ ተሻገር ደግሞ ‹‹ከነበርንበት ችግር ወጥተን ወደ አንድነታችን የምንመለስበት ምቹ አጋጣሚ በመሆኑ ከአሁኑ ጀምሮ የጎንደርን መልካም የሚመኝ ሁሉ በማኅበራዊ ገጾች ጭምር መልካሙንና ስለጥምቀት በዓል አከባበር ሁሉ ያስተዋውቅ፤ የከተማው ሕዝብም ለታሰበው ነገር ስኬት ሠላሙን የማስጠበቅ ሥራውን አጠናክሮ ይቀጥል›› ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ፡- ፍፁምያለምብርሃን ገብሩ -ከጎንደር
ፎቶ፡- ከድረገጽ