የሳዑዲው ንጉሥ ሳልማን 5 ሺህ ለሚጠጉ ሐጃጆች የዒድ አል አድሃ አረፋ ወጪን ሸፈኑ፡፡

35

ባሕር ዳር: ሰኔ 21/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በሐጅ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን የሚጠጋ ምዕመን የተሳተፈበት የዘንድሮው የሐጂ ሥርዓት በቅድስቲቱ ምድር መካ በድምቀት እየተከበረ ነው፡፡

ከመላው ዓለም የተሰባሰቡ የሃይማኖቱ ተከታዮች በተለያዩ ሃይማኖታዊ ሥርዓት በዓሉን እያከበሩ ነው ተብሏል፡፡ የሳዑዲ አረቢያው ንጉሥ ሳልማን የሐጂ ሥርዓትን ለመፈጸም ወደ ቅድስቲቷ ከተማ መካ ለተሰባሰቡት እና ለዓለም ሕዝብ ሙስሊም እንኳን ለዒድ አል አድሃ አረፋ በዓል አደረሳችሁ ብለዋል፡፡

ንጉስ ሳልማን “በታላቁ የሐጂ ሥርዓት እና የአረፋ በዓል ላይ ጎን ለጎን ቆመን የአብሮነትን፣ የወንድማማችነትን እና የአንድነትን ትርጉም እናያለን” ሲሉ በትዊተር ገጻቸው ላይ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ በዚህ በተባረከው የዒድ አል አድሃ አረፋ በዓል ቀን አሏህ የሐጃጆችን ሐጅ እንዲቀበል፣ ለሀገራችን፣ ለመላው ዓለም ሙስሊሞች እና ለቀሪው ዓለም ሕዝብ ኹሉ ሠላምን እና ብልጽግናን እንዲያወርድ እንጸልያለን ነው ያሉት፡፡

በተጨማሪም ንጉሥ ሳልማን በሁለቱ ቅዱስ መስጂዶች የበላይ ጠባቂዎች የሚስተናገዱትን የተወሰኑ ሐጃጆች የዒድ መስዋዕት ወጭ እንደሚሸፍኑ ዓውጀዋል። የንጉሡ ዓዋጅ ተጠቃሚዎች ከ92 ሀገራት የተውጣጡ 4 ሺህ 951 ሐጃጆች ናቸው ተብሏል፡፡

የንጉሡ ዓዋጅ ተጠቃሚዎች በፍልስጤም የሞቱ ሰዎች 1 ሺህ ቤተሰቦቻቸው፣ በዓውሎ ነፋስ ጉዳት የደረሰባቸው እና 2 ሺህ የሚጠጉ የየመን እና ሳዑዲ አረቢያ ወገኖች፣ 280 የሶሪያ ሐጃጆች፣ 150 የመናዊያን የሃይማኖት መሪዎች እና 150 ከአረብ ሊግ የትምህርት፣ የባሕል እና ሳይንስ ድርጅት የመጡ ሐጃጆች ናቸው ሲል የዘገበው ዘ ናሽናል ነው፡፡

በታዘብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየዒድ አል ዓድሃ አረፋ በዓል በአፋር እየተከበረ ነው።
Next articleከፓኪስታን እስከ መካ 4 ሺህ ኪሎ ሜትሮችን በእግሩ በመጓዝ የሐጅ ጉዞውን ያሳካው ወጣት