
ባሕር ዳር: ሰኔ 21/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአረፋ በዓል መገለጫ የኾነው መደጋገፍና መረዳዳት እንዲጐለብት የሃይማኖት አባቶች ኀላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ የታሪክ ተመራማሪው ረዳት ፕሮፌሰር አደም ካሚል ገልጸዋል።
ረዳት ፕሮፌሰር አደም ካሚል እንደገለጹት፣ በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ የሚከበረው የአረፋ በዓል ትልቁ የሐጅ በዓል የሚከበርበት ነው፡፡
አረፋ አደምና ሀዋ የተገናኙበት ነው ያሉት ረዳት ፕሮፌሰር አደም፣ የአረፋ በዓል በአንድ ቦታ በአንድ አለባበስ ከሁለት ሚሊዮን በላይ የእምነቱ ተከታዮች ቋንቋ ሳይገድባቸው፣ ጥቁሩ፣ ነጩ፣ ሁሉም ስፍራና ማንነት ሳያጥረው በአንድነት በመሰባሰብ ጥያቄያቸውን ለፈጣሪ የሚያቀርቡበት ነው ብለዋል፡፡ ፈጣሪም ምህረቴን ሰጥቻችኋለሁ ብሎ የሚያውጅበት ፣ በሐጁ ያልተጋበዙና ዕድሉን ያላገኙ በየሀገራቱ የሚኖሩ በጾም ጊዜውን የሚያሳልፉበት እንደኾነም ጠቁመዋል፡፡ እንደ ተመራማሪው ገለጻ፣ በዓሉ የሰው ልጆችን እኩልነት፣ የመተዛዘን፣ የመከባበር፣ ሥርዓትን የሚያስታውስ ነው፡፡
“ለኢትዮጵያውያን የሐጅ ጉዞ ታሪካችን የምናውቅበት መድረክ ነው፤ ወደ አካባቢው ስንጓዝ እስላማዊ ስደቱ ወደ ኢትዮጵያ የተንቀሳቀስው መቼ፣ የት እንደኾነ ነብዩ ሙሐመድ ለምን የአበሻን ምድር እንደመረጡ፣ እነ ቢላል ማን ናቸው፣ ለምንድነው መሥዋእትነት የከፈሉት፣ በእስልምና የነጃሽ ተሳትፎ ምን ይመስል ነበር የሚለውን በተገቢው ሁኔታ የምንገነዘብበት ነው” ብለዋል፡፡
በሐጅ መድረክ ልክ እንደኮንፈረንስ ኾኖ ኢትዮጵያን የምናስተዋውቅበት ነው ያሉት ረዳት ፕሮፌሰር አደም፣ ነገር ግን እንደ ሀገር ለሀጅ ጉዞ የተሻሉ ምሁራን እንዲሄዱና የኢትዮጵያን ታሪክ በአግባቡ እንዲያስተዋውቁ ከማድረግ አንጻር ውስንነቶችን በመቅረፍ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል።
የአረፋ በዓል የእምነቱ ተከታዮች ጥፋት ካለባቸው ለጥፋቱ ይቅርታ ጠይቀው ወደ ትክክለኛ መንገድ የሚመጡበት ነው ያሉት ረዳት ፕሮፌሰሩ፣ እርስ በእርስ በመተዛዘን ለችግሮች መፍትሄ የሚሰጥበት ትልቅ ሃይማኖታዊ መድረክ እንደኾነም ጠቁመዋል፤ የሐጅ ጉዞ ተንኮልን በመጸየፍ የመተዛዘን፣ የመደጋገፍ ትምህርት የሚቀሰምበት ሃይማኖታዊ ጉዞ እንደኾነም አብራርተዋል፡፡
የታሪክ ተመራማሪው፣ የአረፋ በዓል መገለጫ የኾነው የመደጋገፍና የመረዳዳት ባሕል እንዲጐለብት የሃይማኖት አባቶች ኀላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል። በኢትዮጵያ በሕዝበ ሙስሊሙም ኾነ በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ ያለው ክፍተት ተከታዩ ወደ ቤተ እምነቶች ሲመጣ ብቻ ነው ትምህርት የሚያገኘው። ይህ በቂ ስላልኾነ የሃይማኖት መሪዎች ወደ ታች ወርደው ሊያስተምሩ ይገባል። ሰበካው በቤተ ክህነት እና በመስጅድ መቆጠብ የለበትም። የንግዱም ማኅበረሰብም ኾነ በተለያዩ የሙያ መስኮች ያለው የእምነቱ ተከታይ ሀቀኛ መኾን አለበት። ለዚህም ሃይማኖታዊ ሥርዓቱን ጠንቅቆ እንዲያውቅ ማድረግ አስፈላጊ ነው ብለዋል።
የአረፋ በዓል እርድ አርዶ ለጐረቤት፣ ለዘመድ፣ ለችግረኞች፣ በሰፊው የምናካፍልበት በዓል መኾን እንዳለበት የጠቀሱት ረዳት ፕሮፌሰር አደም፣ ይህ በነቢዩ ኢብራሂም የተሰጠው ትምህርት አንድ ሰው አንድ እርድ አድርጐ አንድ ሦስተኛውን ለራሱ፣ አንድ ሦስተኛውን ለችግረኞች፣ አንድ ሦስተኛውን ለጐረቤት ይሰጣል። ይህም አብሮ መብላትና መካፈልን ያመጣል። ስለዚህ ትምህርቱን በሚገባ ለእምነቱ ተከታዮች ማስተላለፍ ያስፈልጋል ብለዋል።
መረዳዳት በዓል ሲመጣ ብቻ ሳይሆን ሁልጊዜም ባህል ልናደርገው ያስፈልጋል ነው ያሉት። ሰላም፣ መረጋጋትና ልማት እንዲመጣ የሃይማኖት ሊቃውንቶች ትልቅ ሚና አላቸው ብለዋል ረዳት ፕሮፌሰር አደም ካሚል ለኢፕድ በሰጡት ቃለ ምልልስ፡፡
ረዳት ፕሮፌሰር አደም ካሚል ለመላው የእስልምና እምነት ተከታዮችም መልካም የአረፋ በዓል እንዲኾን ተመኝተዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!