“ዓይኖቼ የሚያፈልቁትን የእምባ ዘለላ መቆጣጠር ተስኖኛል፤ ደስታየ ወደር የለውም” የሐጂ ሥርዓት ተካፋይ ያህያ አል ጋናም

59

ባሕር ዳር: ሰኔ 21/2015 ዓ.ም (አሚኮ) 1 ሺህ 444ኛው ዓመተ ሂጅራ የዒድ አል አድሃ አረፋ በዓል በመላው ዓለም ሙስሊሞች ዘንድ በድምቀት እየተከበረ ነው፡፡ ቅድስቲቱ ምድር መካ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የሐጂ ሥርዓት ተካፋይ እንግዶቿን ተቀብላ በተለያዩ ሃይማኖታዊ ዝግጅቶች እያስተናገደች ነው፡፡

የመስዋዕትነት እና የመታዘዝ በዓል የኾነው የአረፋ በዓል በበርካታ ዓለም ሀገራት የሃይማኖቱ ተከታዮች ዘንድ ልዩ ትርጉም አለው፡፡ የጤና እና ገንዘብ አቅማቸው የፈቀደላቸው ሙስሊሞች ቢያንስ በሕይዎት ዘመናቸው አንድ ጊዜ ቅድስቲቱን ምድር መካን በዚህ የሐጂ ሥርዓት ይካፈላሉ፡፡ ሐጂ ያላደረጉ ሙስሊሞች ደግሞ በየሀገራቸው ጠዋት ላይ አደባባይ ወጥተው የዒድ ሶላት ሥርዓትን ያከናውናሉ፡፡

በሐጂ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በዚህ ዓመት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ሐጃጆችን የተቀበለችው ሳውዲ አረቢያ እ.አ.አ ከ2019 በኋላ ከኮሮና ቫይረስ ክልከላ ነጻ የኾነ የሐጂ ሥርዓትን እያከናወነች ነው፡፡ በበዓሉ ከመላው ዓለም የተውጣጡ የሃይማኖቱ ተከታዮች ቅድስቲቱን ምድር ከረገጡ ቀናት ተቆጥረዋል፡፡

ከሐጅ ሥርዓቱ ቀደም ባሉት ቀናት ጀምራ የበዓሉን ዝግጅት በኢግዚቪሽን የጀመረችው ሳዑዲ አረቢያ ለዘንድሮው የዒድ አል አድሃ አረፋ በዓል የነበራት ቅድመ ዝግጅቷ የተሳካ እንደኾነ እየተነገረላት ነው፡፡ ከመላው ዓለም ሀገራት የተሰባሰቡት የእምነቱ ተከታዮች ምድራዊቷን እና የመጀመሪያ የኾነችውን የአሏህ መስጂድ እየዘየሩ ነው ተብሏል፡፡ ከሚና እስከ መካ፤ ከሙዝደሊፋ እስከ አረፋ በተለያዩ ሃይማኖታዊ ቦታዎች የሚደረገው ስግደት እና ጸሎት አስደሳች እንደነበር ከተለያዩ የዓለም ሀገራ በመካ የተሰባሰቡት ሐጃጆች ተናግረዋል፡፡

በዊልቼር የሚንቀሳቀሱት እናቱን ይዞ ከፓኪስታን መካ የገባው ጉል ረህማን “ወላሂ የምትመለከተው ኹሉ አስደሳች ነው” ብሏል፡፡ በመካ ከሚገኘው ታላቁ መስጂድ ካዕባ አካባቢ በዊልቼር ላይ ያሉ እናቱን የሚያስጎበኘው ረህማን የበርካታ ሐጃጆችን እና ዓለም አቀፍ የሚዲያ ሰዎችን ትኩረት ስቧል፡፡

ሐጂ እንደማደርግ ሳስብ የተለየ ስሜት ተፈጥሮብኛል ያለው እና ከግብጽ እንደመጣ የተናገረው የሐጂ ሥርዓት ተካፋይ ያህያ አል ጋናም ባለፉት 15 ቀናት በቀን ከ1 ሰዓት በላይ የተኛሁበትን ቀን አላስታውስም ብሏል፡፡ ወደ ቅድስቲቱ ምድር መካ ከገባሁ በኋላ ያየሁትን ኹሉ ለመናገር ቃል ያጥረኛል የሚለው የሐጂ ሥርዓት ተካፋዩ “ዐይኖቼ የሚያፈልቁትን የእምባ ዘለላ መቆጣጠር ተስኖኛል፤ ደስታየ ወደር የለውም” ብሏል፡፡

አሁናዊ የሙቀት መጠኑ ከፍተኛ ነው በሚባልበት የሳዑዲ አረቢያ እና አካባቢው የሐጂ ሥርዓት ተሳታፊዎች ጃንጥላ እና ውኃ እየተጠቀሙ በዓሉን በደስታ እያከበሩ ነው፡፡ የአካባቢው የአየር ጸባይ ከሀገራቸው የአየር ጸባይ ጋር ፍጹም የተለየባቸው ሐጃጆች ሳይቀር ሙቀቱን ተቋቁመው ሃይማኖታዊ ሥርዓቶችን በደስታ እና በተለየ ስሜት እያከበሩ ነው ሲሉ ዘ ናሽናል እና አልጀዚራ ዘግበዋል፡፡

በታዘብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በተወደደች የዒድ አል አድሃ ቀን የተወደደችውን አድርጉ፤ ስፍር ቁጥር የሌለውን ምንዳም ተቀበሉ፡፡”
Next article“የአረፋ በዓል መገለጫ የኾነው መረዳዳት እንዲጐለብት የሃይማኖት አባቶች ኀላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል” ረዳት ፐሮፌሰር አደም ካሚል የታሪክ ተመራማሪ