
ባሕር ዳር: ሰኔ 21/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በተወደደችው ቀን ተጠበቁ፣ በዚህችም ቀን አንደበታችሁ መልካምን ነገር ተናገሩ። ይህች ቀን የተወደደች ናት፣ ይህችም ቀን ምንዳ የበዛባት፣ ፈጣሪ የሚመሰገንባት፣ እዝነቱ እና ይቅርታ አድራጊነቱ የሚመሰከርባት፣ ትዕዛዝ አክባሪነት፣ ሕግ ጠባቂነት የጸናባት ቀን ናትና በዚህች ቀን ከክፉ ነገር ተጠበቁ፡፡
ነብዩላህ ኢብራሂም የአሏህን ትዕዛዝ አከበረ፣ እስማኤልም የፈጣሪ ፈቃድ ይሁን ሲል ለመሰዋት እሺ አለ፡፡ ፍጹም ፍቅር፣ ፍጹም መታዘዝ፣ ለፈጣሪ መሰጠት የታየባት ቀን ናት፡፡ ይህችን ቀን ማክበር ስፍር ቁጥር የሌለው ምንዳን ታሰጣለች፣ በአሏህ ፊት ታስወድዳለች፡፡ ይህችን ቀን ማክበር ለመሥዋዕት በሚቀርበው በግ ወይም ሌላ የእርድ እንስሳ ጸጉር ልክ ምንዳ ያሰጣል።
በዚህች የዒድ አል አድሃ ቀን መተሳሰብ አለ፣ በዚህች ቀን ለድሃዎች ማዘን አለ፣ በዚህች ቀን የተራበን ማጉረስ፣ የታረዘን ማልበስ፣ የተጠማን ማጠጣት፣ የታመመን መጎብኘት፣ ለአጣ መስጠት አለ፡፡ ትዕዛዝ የተከበረባት እጥፍ ድርብ ምንዳ የተሰጠባት ቀን ናት፡፡ ይህችም ቀን በእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ ትወደዳለች፣ ትከበራለች፡፡
የቻሉ አቅሙ ያላቸው ነብዩላህ ኢብራሂም በእርጅና ዘመናቸው ያገኙትን ልጅ ለመሥዋዕት ወደ አቀረቡበት ቅድስቲቷ ከተማ መካ ይጓዛሉ፡፡ በ9ኛው የዙልሂጃ ቀንም አረፋን በአረፋ ተራራ ያሳልፋሉ።
ወደ መካ መሄድም የተመረጠች ናት፡፡ ያችም ስፍራ ቅዱስ ስፍራ ናትና፡፡ በአሏህ የተመረጠች ነብያት በተደጋጋሚ የጎበኟት ቅዲስ ሥፍራ ናት። ሀጅ ማድረግ አልያም የአሏህንም ቤት መጎብኘት ያልቻሉ በመስጂድ ወይም ሕዝብን በአንድነት በሚያሰባሰብ ሥፍራ ተገናኝተው ለአሏህ ምስጋና ያቀርባሉ፣ አሏህ ለምድር ሰላምና ፍቅርን ይሰጥ ዘንድ ዱዓ ያደርጋሉ፤ የነቡዩ ኢብራሂምን (ዐለይሂ ሰላም) ትዕዛዝ አክባሪነት የእስማኤልንም መልካምነት እና ታዛዥነት ያስባሉ። ከፈጣሪያቸው ከአሏህ ዘንድ ምንዳን አብዝተው ይሻሉ፡፡
በአሁኑ ሰዓት ዒድ አል አድሃ (አረፋ) በዓለም ዙሪያ እየተከበረ ነው፡፡ በባሕርዳር የዒድ አል አድሃ ክብረ በዓል ላይ ዱዓ ያደረሱት እና መልእክት ያስተላለፉት ዶክተር ሼህ ሙሐመድ ከማል ተክቢራ ማድረግ እስከ አምስተኛው አሱር ቀን መከበር አለበት ነው ያሉት፡፡ አደራ የምንለው በዚህ ቀን ወንጀል እንዳንወነጅል፣ በኸይር ቦታ እንድንውል ነውም ብለዋል፡፡ ሸይጣን የሰውን ልጅ ከአሏህ ጋር ለማጣላት ትልቅ ጥረት የሚያደርግበት ቀን ስለኾነ መልካም ነገሮችን በመሥራት ማሰላፍ ይገባናል ነው ያሉት፡፡
ዛሬ የአሏህ ተገዢዎች እና የእርሱ አገልጋዮች መኾናችንን የምናሳይበት ቀን ነውም ብለዋል፡፡ ተዋድደን እንዋል ሲሉም አደራ ብለዋል፡፡
በተወደደች የዒድ አል አድሃ ቀን የተወደደችውን አድርጉ፤ ስፍር ቁጥር የሌለውን ምንዳም ተቀበሉ፡፡
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
📸 አሚናዳብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!