“በዓሉን በፍጹም አንድነት እና በመተሳሳብ ማክበር ይገባል” ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር)

53

ባሕር ዳር: ሰኔ 21/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የዒድ አል አድሃ አረፋ በዓል በባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም በድምቀት ተከብሯል፡፡

በክብረ በዓሉ ላይ የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር)ን ጨምሮ የሃይማኖቱ ከፍተኛ መሪዎች እና የሃይማኖቱ ተከታዮች ተገኝተዋል፡፡

በበዓሉ ላይ መልእክት ያስተላለፉት የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ድረስ ሳህሉ ( ዶ.ር) በዓሉ ሲከበር በፍጹም አንድነት እና መተሳሰብ መሆን አለበት ብለዋል፡፡

ያለው የሌለውን እየረዳ በዓሉን ማክበር እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡ የከተማዋ ሙስሊሞች በአንድነት፣ በመከባባር እና በሰላም እንዲያከብሩ ጥሪ ያቀረቡት ዶክተር ድረስ፤ በዓላት ሲቀርቡ የሚታዩ አንዳንድ ያልተገቡ ምልክቶችን የሃይማት አባቶች በመከካከር እንዲፈቱም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በዓል ሲመጣ መለያየት የለብንም፣ መከባበር፣ መደማመጥ አለብን፣ ተስማምተን መኖር አለብንም ብለዋል፡፡ አባቶች ወጣቶችን በመምከር ያሉ አለመግባባቶችን መፍታት አለባቸውም ብለዋል፡፡ አባቶች በውስጥ መክረው ችግሮችን መፍታት እንደሚገባቸውም አሳስበዋል፡፡

ሁሌም ፍጹም ሰላማዊ የሆነ የበዓል አከባበር እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል፡፡ ከተማዋ በአንድ ሃይማኖት የውስጥ ጉዳይ ይቅርና ልዩ ልዩ ሃይማኖቶች ግጭት የማይፈጥሩባት ከተማ መሆኗን ያነሱት ዶክተር ድረስ፤ የውስጥ ችግሮቹን በውስጥ ለውስጥ ተመካክሮ መፍታት እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡

ዘጋቢ፦ ታርቆ ክንዴ

📸 አሚናዳብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የደስታ ቀን ይሆን ዘንድ የተራበ ቤተሰብን እንዳትረሱ”
Next article“በተወደደች የዒድ አል አድሃ ቀን የተወደደችውን አድርጉ፤ ስፍር ቁጥር የሌለውን ምንዳም ተቀበሉ፡፡”