የመስጂድ አል ሀረም መገኛዋ ቅድስቲቷ መካ ከተማ

82

ባሕር ዳር: ሰኔ 21/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ቅዱስ የኾነችው መካ ከተማ በምዕራብ ሳዑዲ አረቢያ ሂጃዝ ክልል የምትገኝ ከተማ ናት። ነብዩ ሙሐመድ (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) የተወለዱባት እና የቅዱሱ ካእባ መስጅድ መስጂድ አል ሀረም መገኛ ናት።

ከባሕር ጠለል በላይ ከ277 ሜትር ከፍ ብላ የምትገኘው የመካ ከተማ በበጋው ወቅት የሙቀት መጠኗ እስከ 40 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ይደርሳል፡፡

በረሃማው የአየር ሁኔታዋ ግን በየዓመቱ የሚጎበኙዋትን ምዕመናን ቁጥር የመቀነስ አቅም የለውም፡፡ ከሁለት ሚሊየን በላይ ሰዎች እንደሚኖሩባት የሚነገርላትን ቅድስቲቱ ከተማ መካ በዓመት ከ15 ሚሊዮን በላይ የሚደርሱ ምዕመናን ይጎበኟታል፡፡ በነዋሪዎቿ ቁጥር ከዋና ከተማዋ ሪያድ እና ከጂዳ በመቀጠል ሦስተኛዋ የሳዑዲ ከተማ ናት።

በነብዩ ኢብራሂም እንደተመሠረተችም ነው የሚነገረው። ለየመን፣ ሶሪያ፣ ኢራቅ፣ ኢራን እና ለምሥራቅ አፍሪካ በተለይም ደግሞ ለኢትዮጵያ ባላት ስትራቴጅካዊ አቀማመጥ የንግድ ማዕከል እንድትኾን አድርጓታል።

ከቀይ ባሕር በ77 ኪሎ ሜትር የምትርቀው ቅድስቲቷ መካ ከተማ ነጋዴዎች ቅመማቅመም፣ ሽቶ፣ ወርቅ፣ ብርና ሀር የመሳሰሉ ሸቀጦችን ከተለያዩ አካባቢዎች ወደ ከተማዋ ያቀርቡ እንደነበርም በታሪክ ይነገራል።

የአማራ ክልል እስልምና ጉዳይ ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት ሼህ ሙሐመድ አንዋር እንዳሉት መካ በአረቢያ ደሴት ውስጥ የምትገኝ፣ በቁራዓን ስሟ የተጠቀሰች፣ ለሰው ልጆች አላህን እንዲያመልኩ መስጅድ ለመጀመሪያ ጊዜ በመልዓክቶች አማካይነት የተሠራባት ቦታ ናት፤ አደም ሰባት ጊዜ ተመላልሰው የጎበኟት ቅድስት ስፍራም ናት፡፡

ሼህ ሙሐመድ እንዳሉት ነብዩላህ ኑህ (ዐለይሂ ሰላም) ከአሏህ ውጭ የሚመለክ የእውነት አምላክ እንደሌለ በሚያስተምሩበት ጊዜ ሕዝቡ በማመጹ አሏህ ዓለምን በጎርፍ ሲቀጣ ከጥፋት የተረፈች ቅዱስ ቦታ ናት፤ ነብዩ ኢብራሂም ልጃቸውን እና ባለቤታቸውን ይዘው ወደ መካ እንዲጓዙ በአሏህ የታዘዘባት ቦታም ናት።

ነብዩ ኢብራሂም የአሏህን ትእዛዝ ተቀብለው ሚስታቸውንና ልጃቸውን በምድረ በዳዋ ምድር ተዋቸው። አሏህም እምነታቸውን አይቶ መልዓክትን ልኮ የምንጭ ውኃ እንዲፈልቅ አደረገላቸው። የነብዩላህ ኢብራሂም ባለቤት የኾኑት ሀጀር እና ልጃቸው ኢስማኤልም በዘምዘም ውኃ አጠገብ ተቀመጡ። እነሱን ተከትሎም ሌሎች ሰዎች ተቀላቅለው መኖር እንደጀመሩ ገልጸዋል። በሙሳ፣ በኢሳ እና በሌሎች ነብያቶችም የተጎበኘች ቅዱስ ቦታ እንደኾነች ገልጸዋል፡፡

በመኾኑም አሏህ ለመጀመሪያ ጊዜ በመላእክቶች አማካይነት የአምልኮ ቦታ ያሠራባት ቦታ መኾኗ እና ነብዩ ኢብራሂም ካዕባን ገንብተው ሲጨርሱ ሰዎች በቻሉት ሁሉ ወደዚህ ሥፍራ እንዲመጡ ጥሪ እንዲያደርጉ እና ቤቱ እንዲጎበኝ አሏህ ያዘዘበት ቦታ በመኾኑ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሙስሊሞች ከአራቱም የዓለም ማእዘናት ወደ ቅዱሷ ከተማ መካ በየዓመቱ ሀጅ ለማድረግ ይጎርፋሉ።

ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“አንድን ነገር ትጠሉት ይኾናል ያ ነገር በጎ ኾኖ ሳለ፣ አንድን ነገር ትወዱት ይኾናል ያ ነገር ለእናንተ መጥፎ ኾኖ ሳለ”
Next article“የደስታ ቀን ይሆን ዘንድ የተራበ ቤተሰብን እንዳትረሱ”