“አንድን ነገር ትጠሉት ይኾናል ያ ነገር በጎ ኾኖ ሳለ፣ አንድን ነገር ትወዱት ይኾናል ያ ነገር ለእናንተ መጥፎ ኾኖ ሳለ”

54

ባሕር ዳር: ሰኔ 21/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ደጋግ ልቦች ፈጣሪያቸውን ይታዘዛሉ፣ ሕግጋቱን ያከብራሉ፣ ትዕዛዙን ይጠብቃሉ፣ ጠብቀው ያስጠብቃሉ፣ መልካም ልቦች ፈጣሪያቸውን ከሁሉ አስበልጠው ይወዳሉ፣ በፍቅሩ ውስጥ ይኖራሉ፣ ስለ ፍቅሩ ለመሥዋዕት ይዘጋጃሉ፤ መንገዳቸውን በፈጣሪ ፈቃድ ያዘጋጃሉ፣ በተፈቀደላቸውም መንገድ ይጓዛሉ፡፡

ደጋግ ልቦች በምድር ለሰማዩ ቤታቸው ይዘጋጃሉ፣ የመጭው ዓለም ቤታቸውንም በመልካም ሥራቸው ይሠራሉ፤ የአምላካቸውን ስም እየጠሩ ምሥጋና ያቀርባሉ፣ ለእርሱ የተገባውን ሁሉ ያደርጋሉ፣ እርሱ የፈቀደውንም ይፈጽማሉ፣ በእርሱ ዘንድ ያልተፈቀደችውን፣ በእርሱም ዘንድ የተጠላችውን ከአጠገባቸው ያርቃሉ፣ መልካም ያልኾነችውን ይሸሻሉ፡፡

ትዕዛዙን ያከበሩት ስማቸው በትውልድ ሁሉ ይወሳል፣ በመልካም መዝገብ ላይ ተጽፎ ይነሳል፡፡ ትዕዛዙን ያከበሩት በፈጣሪያቸው የላቀውን ምንዳ ይቀበላሉ፡፡ በእርሱም ፊት የተወደዱና የተከበሩ ይኾናሉ፡፡ ነቢዩላህ ኢብራሂም ትዕዛዙን አክብረዋልና ተከበሩ፣ የላቀውን ምንዳም ተቀበሉ፡፡ የአባቱን ትዕዛዝ ይሁን፣ ይደረግ፣ እኔም ከታጋሾች ዘንድ እንድኾን ከተፈቀደ ያለው እስማኤልም ከፍ ያለውን ምንዳ ተቀበለ፡፡

ዒድ አል አድሃ ደርሷል፡፡ ኢድ አል አድሃ በደረሰ ጊዜም የአሏህ ትዕዛዝ ሰጪነት፣ የኢብራሂም እና የልጃቸው የእስማኤል በፍጹም ፍቅር ትዕዛዝን ተቀባይነት እና ፈጻሚነት ይነሳል፡፡ እነርሱ ትዕዛዝን ተቀብለዋል፣ የአምላካቸውን ቃል አክብረዋልና፣ የእርሱ ትዕዛዝ አክባሪነት እየታወሰ፣ ለፈጣሪ ምሥጋና ይቀርብበታል፡፡ ስለ ደግነቱ እና ስለ ኀያልነቱ ይነገርበታል፡፡ ዒድ አል አድሃም የኢብራሂምን እና የእስማኤልን ትዕዛዝ አክባሪነት እና ፍጹም የፈጣሪ ፍቅርን ያሳዩበትን መነሻ በማድረግ የሚከበር ነው፡፡

በተውፊቅ ፍልውኃ መስጅድ ኢማም ዑዝታዝ ባሕሩ ዑመር ዒድ አል አድሃ በዓል ከኢብራሂምና ከልጃቸው ከእስማኤል ታሪክ ጋር የሚነሳ ነው ይላሉ፡፡ የነብዩ ሙሐመድ (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) ባልደረቦች ይህን በዓል ስለምን እናከብረዋለን? በማለት ነብዩ ሙሐመድን በጠየቋቸው ጊዜ ይህ የአባታችሁ የኢብራሂም ሱና ነው አሏቸው፡፡ ይህን በማድረጋችንስ ምን እናገኛለን? ብለውም ጠየቋቸው በምታርዱት በግ ወይም ሌላ የእርድ እንስሳ ፀጉር ልክ ምንዳ ታገኛላችሁ አሏቸው፡፡ ዒድ አል አድሃም ስፍር ቁጥር የሌለው ምንዳ የሚገኝበት ታላቅ በዓል ነው፡፡

በመላው ዓለም የሚገኙ ሙስሊሞችም ይህን ከአምላክ ዘንድ ምንዳ የሚገኝበትን በዓል በመታመን ያከብሩታል፣ ምንዳም ይቀበሉበታል፡፡ ነቢዩላህ ኢብራሂም ልጃቸውን ለመሥዋዕት ማቅረብ እንዳለባቸው ከፈጣሪ ትዕዛዝ ሲደርሳቸው በሕልም ያያሉ፡፡ በእስልምና ሃይማኖት አስተምህሮ የነብያት ሕልም እንደ ራዕይ ይታያል፡፡ ኢብራሂምም ለልጃቸው ለእስማኤል በሕልሜ አንተን እረድ ተብዬ ሳርድህ አየሁኝ፣ ይህም የፈጣሪ ትዕዛዝ ነው ምን ትላለህ ልጄ? ብለው ጠየቁት፡፡ እስማኤልም አባቴ ሆይ የታዘዝከውን ሥራ፣ ፈጣሪ ያዘዘህን ከመፈጸም ወደኋላ እንዳትል፣ እኔም ከታጋሾቹ እሆን ዘንድ አሏህ ከፈቀደ አላቸው ነው ያሉኝ ዑዝታዝ ባሕሩ፡፡

አባትና ልጅ የፈጣሪያቸውን ትዕዛዝ ተቀበሉ፡፡ ነቢዩ ኢብራሂምም ትዕዛዙን ይፈጽሙ ዘንድ በእርጅና ወቅት ያገኙትን ልጃቸው እስማኤልን ለመሠዋት ወደ መሠዊያው ወሰዱት፡፡ የአባት አንጀት ኾኖባቸው መሥዋእትነቱን እንዳይተዉ ልጃቸው ፊቱን ወደ መሬት ደፍተው ይሠውት ዘንድ ጠየቃቸው፡፡ እርሳቸውም ያን አደረጉ፡፡ በዚህም ጊዜ ይላሉ ዑዝታዝ ባሕሩ እስማኤልን ለመሠዋት የተሳለች ቢላዋ እንቢ አለች፡፡ ይህም የኾነው በአሏህ ኀይል እንጂ በእርሷ ፈቃድ አልነበረም፡፡

መልአኩ ጅብሪልም ከሰማይ መጣ፡፡ ኢብራሂምም ድምጽ ደረሳቸው፡፡ ሕልምህን እውን አድርገሃል፡፡ ልጅህን ለመሥዋዕት አቅርበሃል፡፡አሁን እጅህን አንሳ አላቸው፡፡ በልጃቸው ፈንታ ለመሥዋዕት በግ ተሰጣቸው፡፡

ነቢዩ ኢብራሂም ትዕዛዝን ያከብራሉ፡፡ ከልጁና ከእኔ ፍቅር የትኛውን ያስበልጣል ብሎ ሊፈትናቸው በወደደ ጊዜ ፈጣሪ ልጅህን ሠዋልኝ አላቸው፡፡ ኢብራሂምም የአምላክን ፍቅር አስበለጡና ትዕዛዙን ተቀበሉ፡፡ ልጃቸውንም ለመሥዋዕት አቀረቡ፡፡ ፈጣሪም ነቢዩ ኢብራሂምን ወደደው፡፡ ነቢዩ ኢብራሂም (ዐለይሂ ሰላም) ታላቁን ፈተና አለፉት፡፡ ፈጣሪያቸውን አብዝተው ወደዋልና በፈጣሪያቸው ዘንድ ተወደዱ፡፡

ኢብራሂም ብቻ ሳይኾኑ ልጃቸው እስማኤል ታዛዥነቱን አሳይቷል፡፡ ፈቃዱን ፈጽሟል፡፡ ከዚያም ወዲህ የኢብራሂምን እና የእስማኤልን መንገድ የሚከተሉ ሁሉ ይህን የመሥዋዕት ቀን እየጠበቁ ዒድ አል አድሃን ያከብራሉ፡፡ ከፈጣሪያቸውም ምንዳ ይቀበላሉ፡፡ ፈጣሪ ፈተናዎችን ሲያመጣ የፈጠራቸውን ሊያከስር ሳይኾን የበለጠ ሊጠቅም ነውም ይላሉ ዑዝታዝ ባሕሩ፡፡ ፈጣሪ የሚጎዳ ፈተና አያመጣም፡፡ ለእርሱ ታማኞች እና ተገዢዎች መኾናችንን ለማረጋገጥ ፈተና ያመጣል እንጂ ነው ያሉት፡፡

አንድን ነገር ትጠሉት ይኾናል ያ ነገር በጎ ኾኖ ሳለ፣ አንድን ነገር ትወዱት ይኾናል ያ ነገር ለእናንተ መጥፎ ኾኖ ሳለ ተብሏል፤ ፈጣሪም የሚጠቅመውን እንጂ የማይጠቅመውን አያደርግም ነው ያሉኝ ዑዝታዝ ባሕሩ፡፡

አሏህ ከኢብራሂም እና ከእስማኤል የፈለገውን ስላገኘ መሥዋዕትነቱ እንዳይፈጸም፣ እስማኤል ሞቶ ኢብራሂም እንዳያዝኑ እና ልባቸው እንዳይሰበር ለመሥዋዕት የሚኾን ሰጣቸው፡፡ የአምላካቸውን ትዕዛዝ የሚያከብሩና የሚፈጽሙም እነርሱ ከሚሰጡት በብዙ አጥፍ የላቀ ወሮታ እንደሚያገኙ ያስተማረበት ቀንም ነው፡፡ ትዕዛዝን አለማክበር ግን የፈጣሪን ቁጣ ያመጣል ነው ያሉኝ፡፡

ሰው የፈጣሪን ትዕዛዝ ባከበረ ቁጥር ከፍ ይላል፡፡ ልጆች የወላጆቻቸውን ትዕዛዝ ያከብራሉ፡፡ የወላጆቻቸውን ትዕዛዝ የማያከብሩ ደግሞ ወደ አልተፈለገ ቦታ ይሄዳሉ፡፡ የትናንት መሠረት ሲጠፋ የዛሬ ትውልድ መሠረት ያጣል፣ ትናንትን መጠበቅ እና የትናንትን መልካም ታሪክ መሠረት ማድረግ መልካም ትውልድ ይኾን ዘንድ ያደርገዋል ነው ያሉት፡፡ የታሪክ መሠረት የሌለው ግን ምንም ነው፡፡ ለወላጆቹ ክብር ያልሰጠ ልጅ ለሀገሩ፣ ለሃይማኖቱ፣ ለወገኖቹ ክብር አይኖረውም፡፡ ወላጆቹን የማያከብር፣ የትናንት የታሪክ መሠረት የሌለው ሀገሩን የሚሸጥ፣ ለሃይማኖቱም ግድ የለሽ ይኾናል ነው ያሉኝ፡፡

በኢትዮጵያ ልጆች ለወላጆቻቸው ብቻ ሳይኾን ለጎረቤትም የሚታዘዙበት፣ ጎረቤታቸውንም የሚያከብሩበት መልካም ባሕል እንዳለ ያነሱት ዑዝታዝ ባሕሩ አሁን አሁን ላይ ይህ መልካም ባሕል እየቀነሰ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡ ታዛዥነትን እና ማክበርን መጠበቅ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡ ወላጆች ልጆቻቸውን በመልካም ባሕሪና ሥነ ምግባር ማሳደግ እንደሚገባቸውም ተናግረዋል፡፡ የሃይማኖት መሪዎችም መታዘዝን ማስተማር አለባቸው ነው ያሉት፡፡ መታዘዝ በፈጣሪ ዘንድ ታላቅ ምንዳ የሚያሰጥ መኾኑን ማስተማርና ማሳወቅ ይገባል ብለዋል፡፡

አሏህ ለአባትና ለእናትህ መልካም ውለታን ዋልላቸው፣ በንግግርም ቢኾን የማይኾን ንግግር አትናገራቸው፣ ለእነርሱ ትሁት ሁንላቸው፣ ለእነርሱም እንዘንላቸው ብሏል ነው ያሉኝ፡፡ እኔንም አመሥግን እነርሱንም ተንከባከባቸው፣ ስለ ውለታቸውም አመሥግናቸው ይላል ብለውኛል፡፡

ልጆች ከወላጆቻቸው ፊት ሲቀመጡ በአደብ ከመቀመጥ ጀምሮ፣ ንግግራቸውን መስማት፣ ትዕዛዛቸውን ማክበር ይገባቸዋልም ነው ያሉኝ፡፡ ዒድ አል አድሃ መተዛዘን ያለበት፣ ፈጣሪ የሚመሠገንበት ነው፣ ነብዩ ሙሐመድም (ሰ.ዐ.ወ) በዒድ አል አድሃ ኡድሂያ በምታርዱበት ወቅት ሰደቃ ስጡ ብለዋልና፣ ችግረኛ ወገኖችን መርዳት መረሳት የለበትም ነው ያሉት፡፡

የታዘዙት ሁሉ መልካምን ያገኛሉ፤ ለመሥዋዕት ካቀረቡት በእጅጉ የላቀ ምንዳ ይቀበላሉ፡፡ ምንዳውም ዘመን የሚሽረው፣ እድሜ የሚያጠወልገው አይደለም፡፡ በፈጣሪ ዘንድ ሕያው ኾኖ ይኖራል እንጂ፡፡ በሰው ዘንድም ሲነገርና ሲዘከር ይኖራል፡፡ ትዕዛዛቱን አክብሩ፣ መልካሙን ነገርም አድርጉ፡፡

በታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“እንኳን ለዒድ አል አድሃ በዓል አደረሳችሁ!” ርእሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር)
Next articleየመስጂድ አል ሀረም መገኛዋ ቅድስቲቷ መካ ከተማ