
ባሕር ዳር፡ ሕዳር 25/2012ዓ.ም (አብመድ) ሙስናና ብልሹ አሠራርን ለመከላከል በሀገር አቀፍ ደረጃም ሆነ በአማራ ክልል ተቋማዊ የመከላከል ስትራቴጂ ተቀርጾ ወደ ሥራ ተገብቷል፡፡ በአማራ ክልልም 18 ቋማት በተለዬ መልኩ ስትራቴጂውን ተግባራዊ እንዲያደርጉ ኃላፊነት ተሰጥቷቸዋል፡፡ በየተቋማቱ ላሉ ሠራተኞች የሥነ-ምግባር ትምህር እንዲሰጡ፣ ለሙስና ተጋላጭነት የሚጨምሩ ነገሮችን በመለየትና ጥቆማዎችን ተቀብለው በማጣራት ለሕግ የሚያቀርቡ የሥነ ምግባር መኮንኖች መዋቅርም ተፈቅዶላቸዋል፡፡
ይሁን እንጂ ተቋማት ለሙስና አጋላጭ የሆኑ ምክንያቶችን ለይቶ የመከላከል ውስንነት እንዳለባቸው ነው የአብክመ ሥነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ዝግአለ ገበየሁ የተናገሩት፡፡ እንደ ኮሚሽነሩ ገለጻ ከ18 ተቋማት መካከል ኃላፊነታቸውን በሚገባ የተወጡት ዘጠኙ ብቻ ናቸው፡፡ በአማራ ክልል ያለው የሙስናና ብልሹ አሰራር የመከላከል ሥራ ውጤታማ አለመሆኑንም አቶ ዝግአለ ነግረውናል፡፡
ሙስናና ብልሹ አሠራር የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችን ተሳትፎ የሚጠይቅ ቢሆንም ኃላፊዎች በሌሎች አጀንዳዎች ተጠምደው ለጉዳዩ ትኩረት አለመስጠታቸው፣ የማኅበረሰቡ የኅልውና አደጋ የሆነውን ሙስናን ለመከላከል ምቹ ሁኔታ አለማግኘታቸው፣ በኮሚሽኑ ኅብረተሰቡን ተደራሽ የሚያደርግ አደረጃጀት አለመኖሩ እና የፖለቲካ አለመረጋጋቱ የመከላከል ሥራው ውጤታማ ላለመሆኑ በምክንያትነት ተጠቅሰዋል፡፡ የማኅበረሰቡ የሥነ ምግባር እሴቶች መሸርሸር እንዲሁም የምርመራ እና የዐቃቤ ሕግ ሥራው ለሌሎች ተቋማት ተላልፎ መሰጠቱን ተከትሎ ሙስናን የመከላከል ሥራው እንደቆመ አድርጎ መቁጠርም ለሙስናና ብልሹ አሠራር መስፋፋት በምክንያትነት ተነስተዋል፡፡
ሙስናና ብልሹ አሠራርን ከመሠረቱ ለመቅጨት መንግሥት እና ሕዝብ ትኩረት እንዲሰጡት ማድረግ፤እንዲሁም ሕጻናትን እና ወጣቶችን በሥነ ምግባር ገንብቶ ማስተማር እና ማሳደግ ዋነኛው አማራጭ መሆኑን ኮሚሽነሩ ተናግረዋል፡፡ የሥነ-ምግባር ግንባታ ስትራቴጂውን ተግባራዊ ለማድረግም በክልሉ ከሚገኙ የትምህርት ተቋማት ጋር ለመሥራት የተጀመሩ እንቅስቃሴዎች መኖራቸውን አስታውቀዋል፡፡
የሃይማኖት ተቋማትን በማሳተፍ፣ ከተለያዩ የሙያና የሲቪክ ማኅበራት እንዲሁም ከተለያዩ አደረጃጀቶች ጋር ፎረም በማዘጋጀትም የሙስናን ምንነት፣ መንስኤዎች፣ የሚያስከትለውን ጉዳት እና መከላከያ መንገዶችን ለኅብረተሰቡ ግንዛቤ መፍጠር ሙስናን ለመከላከል ከተያዙት እቅዶች መካከል አንዱ ነው፡፡ የተሸረሸሩትን የሕዝብ እሴቶች ወደነበሩበት መመለስ ዋነኛው የሙስና እና ብልሹ አሠራር መታገያ በመሆኑ ቀደምት እሴቶችን መመለስ በትኩረት ይሠራበታል ብለዋል፡፡
የምርመራ እና የክስ ተግባር ከተሰጣቸው የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን እና ዐቃቤ ሕግ ጋር በቅንጅት እንደሚሠራም አስታውቀዋል፡፡ ባሕሪያቸው ለሙስናና ብልሹ አሠራር ተጋላጭነትን የሚጨምሩ እንደ መሬት አስተዳድር፣ የመንግሥት ግዥ፣ ፍትሕ፣ ገቢ ሰብሳቢ እና ሌሎች ተቋማትን ኮሚሽኑ ልዩ ትኩረት በመስጠት የሚሠራባቸው መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡ የየተቋማት መሪዎች ተቋማዊ፣ ሞራላዊ፣ ሕጋዊ ግዴታ እና ኃላፊነት ስላለባቸው የሚመሩት ተቋም ከሙስና የጸዳ እንዲሆን በትኩረት መሥራት እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡
ኮሚሽኑን በቂ መዋቅራዊ አደረጃጀት ሳይኖረው ሲሠራ መቆየቱን ያመላከቱት አቶ ዝግአለ አደረጃጀቱን በማጠናከር ብልሹ አሠራርን ለመታገል እየተሠራ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡ ለሥራው 431 ባለሙያዎች እንደሚያስፈልጉ እና ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ 230 የሥነ ምግባር መኮንኖች መመደባቸውንም አስታውቀዋል፡፡ እንደ አቶ ዝግአለ ገለጻ አደረጃጀቱን የማስተካከል ሥራው ቀጣይም ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል፡፡
ሙስና የሀገርን ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ፣ ሥነ ልቦናዊ እና ተቋማዊ አደረጃጀት ችግር ውስጥ የሚጥል በመሆኑ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ችግሩን በጋራ ለመከላከል እንዲችል ሕዳር 30/ 1996 ዓ.ም የዓለም ሀገራት ተሰባስበው ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በጠቅላላ ጉባዔው ስምምነቱን ሲያጸድቅ አባል ሀገራት እንዲሳተፉ ክፍት የሆነበት ቀን ዓለም አቀፍ የጸረ ሙስና ቀን ሆኖ እንዲከበር ውሳኔ አሳልፏል፡፡
በዚህም መሠረት ቀኑ በዓለም አቀፍ ደረጃና በኢትዮጵያ ደረጃ ተከብሮ ይውላል፡፡ በአማራ ክልልም ቀኑ በልዩ ልዩ ዝግጅቶች ተከብሮ እንደሚውል ኮሚሽነር ዝግአለ ተናግረዋል፡፡ ሲከበርም የሥነ-ምግባር ግንባታ እና የሙስና እና ብልሹ አሠራር መከላከል ሥራ ተግባራዊ ማድረግ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ በመምከር እንደሚሆን ነው ያስታወቁት፡፡ የየቢሮው ኃላፊዎች እና ምክትል ኃላፊዎች እንዲሁም አጋር እና ባለድርሻ አካላት በተገኙበት የፓናል ውይይት፣ ስፖርታዊ ውድድሮችና በጥያቄና መልስ የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ በመሥራት ቀኑ እንደሚከበር ነው የተገለጸው፡፡
ዘጋቢ፡-ደጀኔ በቀለ