“ታላቅ ታሪክ ያለበት፣ መልእክተኞች ያረፉበት”

50

🕌 ልዩ ጥንቅር 🕋
ባሕር ዳር: ሰኔ 20/2015 ዓ.ም (አሚኮ) እነሆ በዚያ ዘመን ፍትህ የበዛባት፣ ሰላም የመላባት፣ ፍትሕ አዋቂ፣ ደግ አድራጊ ንጉሥ የነገሠባት፣ ሕዝብ ሁሉ በደስታና በፍቅር የሚኖርባት፣ ሰው ሁሉ በሰውነቱ የሚከበርባት፣ ንጉሡ መልካም ነገር የሚያደርጉባት፣ የተወደደችን ፍርድ የሚፈርዱባት ሀገር ከሁሉም ልቃ ተገኘች፡፡ ከኃያላኑ ሁሉ ትበልጣለች፣ ከነገሥታቱ ሁሉ የበለጠውን ደገኛውን ንጉሥ አንግሳለች፡፡ ከተወደዱትም በልጣ ተወዳለች፣ ከተመረጡትም በልጣ ተመርጣለች፡፡

ስሟ በዓለሙ ሁሉ ይጠራል፣ ኃያልነቷ በሕዝቡ ሁሉ ይወራል፣ ከእርሷ የከበረው ማዕድን ይጫናል፣ የብስ የሚያቋርጡ፣ ባሕር የሚሰነጥቁ፣ ከቀያቸው ርቀው የሚከርሙ፣ ነግደው የሚያተርፉ፣ ከሀገር ሀገር እየተዘዋወሩ፣ አንደኛውን ከሌላኛው ጋር የሚያገናኙ ነጋዴዎች ይወዷታል፣ መዳረሻቸው ትኾን ዘንድ ይመርጧታል፡፡ የተወደደች ናትና የተወደደችውን ይዘው ይከትሙባታል፣ የተወደደውን ነገርም ይሸምቱባታል፣ ከተወደደው ሕዝብ ጋር ይከርሙባታል፡፡ የተከፉት የሚጽናኑባት፣ የተራቡት የሚጎርሱባት፣ የተጠሙት የሚጠጡባት፣ የታረዙት የሚለብሱባት፣ መጠለያ ያጡት የሚጠጉባት፣ ቀን የገፋቸው ቀን የሚያሳልፉባት፣ የልባቸውን መሻት የሚፈጽሙባት ታላቅ የኾነች፣ ታላቅ ንጉሥ ያነገሠች፣ ታላቅ ታሪክ ያላት፣ የጠበቀና የተወደደ ሥርዓተ መንግሥት ያለባት፣ ሰው ከሰው የሚዋደድባት እና የሚተሳሰብባት ሀገር ነበረች፡፡

ደጋጎች ይወዷታል፣ በምድሯ ይመላለሱባታል፣ በዋሻዎቿ፣ በተራራዎቿ፣ በሜዳና በሸለቆዎቿ ይኖሩባታል፣ ደግነትንም ያደርጉባታል፡፡ ሃይማኖተኞች የሚማጸኑባት፣ ከፈጣሪያቸው በረከት እና ምንዳ የሚቀበሉባት፤ የደጋጎች ምድር ናትና ትወደዳለች፣ የብልሆች ምድር ናትና ትመረጣለች፡፡ የታማኞች ምድር ናትና ለክፉ ቀን ትታመናለች፣ ፍትሕ የሚያውቁ ሕዝቦች የሚኖሩባት፣ ፍትሕ የሚያውቅ፣ መልካምም የሚያደርግ ንጉሥ የነገሠባት ናትና ፍትሕን ባጡ ሰዎች ትመረጣለች፡፡

በዚያ ዘመን ነብዩ መሐመድ ( ሰ.ወ.ዐ) ፈጣሪ መርጧቸው ተነሱ፡፡ ነብይም አድርጓቸዋል፡፡ ጣዖት በበዛባት፣ ደሃ በማይከበርባት በዚያች ምድር ተነስተው፣ ከአሏህ የተሰጣቸውን ትዕዛዝ መፈጸም ጀመሩ፡፡ አስተምህሯቸው ከተለመደው የተለየ ነበርና ገሚሶች ወደዷቸው፣ ቃላቸውን ሰምተውም ተከተሏቸው፡፡ ነገሥታትና በተንደላቀቀ ሕይዎት የሚኖሩት ግን በዓይነ ቁራኛ ተመለከቷቸው፡፡ ይባስ ብለው አሳደዷቸው፡፡ እሳቸውን ብቻ ሳይኾን የእርሳቸውን አስተምህሮ የተከተሉትን አሳደዷቸው፡፡ በዚህም ወቅት ነብዩ መሐመድ (ሰ.ወ.ዐ) ሰላም እስኪገኝ የአሏህን ቃል በነጻነት የሚያስተምሩበትና ትዕዛዛቸውን የሚፈጽሙበት ጊዜ እስኪመጣ ድረስ ተከታዮቻቸውን ከዚያች ምድር ማራቅ ፈለጉ፡፡ እሳቸውም ደገኛ ንጉሥ የነገሠባት፣ ፍትሕና ሰላም የበዛባት ምድር እንዳለች ያውቁ ነበርና ተከታዮቻቸው ወደ ዚያች ምድር ይሄዱ ዘንድ አዘዟቸው፡፡ ያቺም ምድር የሐበሻ ምድር ኢትዮጵያ ናት፡፡ ነብዩ መሐመድ ( ሰ.ወ.ዐ) ከኢትዮጵያ የቀረቡ ሀገራት እንዳሉ ያውቃሉ፡፡ እነዚያ ምድር ግን ከኢትዮጵያ ተሽለው አልተገኙም ነበር፡፡ በልባቸው የተወደደች እና የተመረጠች ምድር ኢትዮጵያ ነበረችና ኢትዮጵያን ለተከታዮቻቸው መረጧት፡፡ ተከታዮቻቸውም የነብያቸውን ትዕዛዝ ተቀበሉ፡፡ የተባለውንም አደረጉ፡፡

ፍትሕ የሚያውቅ ንጉሥ በታላቋ ሀገር ነግሦ ነበርና ከነብዩ መሐመድ (ሰ.ወ.ዐ) የተላኩትን መልእክተኞች በሰላም ተቀበሏቸው፡፡ በክብርም ይኖሩ ዘንድ ፈቀደላቸው፡፡ ይህም ንጉሥ ነጋሲ ( ነጋሺ፣ ነጃሺ) የተሰኘው ነው፡፡ በተውፊቅ ፍልውኃ መስጅድ ኢማም ዑዝታዝ ባሕሩ ዑመር ይህንን ታሪክ ሲነግሩኝ፤ በነብዩ መሐመድ (ሰ.ወ.ዐ) አምስተኛው ነብይነት ረጀብ በተሰኘው ወር ላይ ሙስሊሞቹ በመካ እስልምናን ሲቀበሉ እንግልትና መሳደድ በዛባቸው፡፡ አንድ ላይም ተሰብስበው ዱዓ ማድረግ አልቻሉም፡፡ መከራው ሲጸናባቸውም ነብዩ መሐመድ ተከታዮቻቸውን ሂዱ ወደ ሃበሻ ምድር አሏቸው ነው ያሉኝ፡፡ በዙሪያቸው ፋርሶች፣ ሮማውያን አሉ፡፡ ሐበሻ ግን ባሕር ተሻግረው ነው የሚያገኗት፡፡ ነብዩ ግን ባሕር ተሻግረው የሚያገኗትን የሐበሻን ምድር መረጡ፡፡

በዘመኑ የአክሱም ስልጣኔ ገናና የነበረበት ነበር፡፡ በዘመኑ ገናና ከነበሩ መንግሥታት መካከል አንደኛው የነበረው የኢትዮጵያ መንግሥት እስከ የመን ድረስ ተሻግሮ ያሥተዳድር ነበርና ታሪኩ ቅርብ ነው፡፡ እሳቸውም ወደ ሌሎች ሀገር ሂዱ ከማለት ይልቅ ሰላም እስኪመጣ ድረስ ወደ ሐበሻ ምድር ሂዱ አሏቸው ነው ያሉኝ፡፡ በዚያ ብትሄዱ ማንም የማይበደልበት ፍትሐዊ ንጉሥ አለ አሏቸው፡፡ እነርሱም ነጋሲ (ነጃሺ) ነግሰው ወደ ሚያስተዳድሯት ወደ ሐበሻ ምድር መጡ፡፡ ለመጀመሪያም ጊዜ አሥራ ሁለት ወንዶች እና አራት ሴቶች ኾነው ነበር የመጡት፡፡ መጀመሪያ ከመጡት መካከልም በእስልምና ታሪክ ሦስተኛው ከሊፋ የሚባሉት ኡስማን ኡብኑ አፋን ይገኙበታል፡፡ እነርሱም የመጡበት ዘመን አምስተኛው የነብይነት ዓመት በረጀብ ወር ነበር፡፡ ወደ ሐበሻ ምድር በመጡ ጊዜም ንጉሡ በሰላም እንዲቀመጡ አደረገ ነው ያሉኝ፡፡

እነዚህ የነብዩ መሐመድ መልእክተኞች ወደ ሐበሻ ምድር በመጡ በሦስተኛው ወር በመካ ያሳደዷቸው ሰዎች እስልምናን ተቀብለዋል የሚባል ወሬ ሰሙ፡፡ ከሐበሻ ምድርም ተነስተው ወደ ተነሱባት የመካ ምድር ገሰገሱ፡፡ ነገር ግን የተባለው ልክ አልነበረም፡፡ ለሁለተኛውም ጊዜ ከበፊቱ በርከት ያሉ ሰዎች ኾነው ወደ ሐበሻ ምድር መጡ ነው ያሉኝ፡፡ እነርሱ በመጡ ጊዜ የእናት እና የአባቶቻቸውን ሃይማኖት ጥሰው የመጡ ናቸው፣ ከአንተ ሃይማኖት ክርስትናም አልገቡም፣ ስለዚህም ወገኖቻችን ልከውን ልንወስዳቸው መጣን የሚሉ መልእክተኞች ወደ ሐበሻው ንጉሥ ዘንድ ቀረቡ፡፡

ንጉሡ ግን ዝም ብዬ አልሰጣችሁም አለ፡፡ ንጉሡም መልእከተኞችን ጠየቀ፡፡ እምነታቸውንም ነገሩት፡፡ አሏህን እንደሚያመልኩ፣ ለጣዖት እንደማይሰግዱ፣ ከፈጣሪ በቀር ሌላ አምላክ አታምልኩ የሚል ትዕዛዝ እንደመጣላቸው፣ ድሃዎችን እንደማይበድሉ፣ ለሰዎች እንደሚያዝኑ፣ መልካምን ነገር እንደሚያደርጉ ነገሩት፡፡ በዚያች ምድር ሰዎች በደሉን፣ ጨቆኑን፣ የአንተን ፍትሐዊነት አይተንም መጣን አሉት፡፡ ይህን በሰማ ጊዜ የነብዩን ባልደረቦች ሊወስዱ የመጡትን ሰዎች መልሶ ላካቸው፡፡ የነብዩን ባልደረቦች ግን እናንተ የተከበራችሁ ናችሁ፣ በዚህ ምድር የሚነካችሁ የለም፣ በሰላም ኑሩ ብሎ ፈቀደላቸው ነው ያሉኝ ዑዝታዝ ባሕሩ፡፡

ኢትዮጵያ ፍትሕ በጠፋበት ጊዜ ፍትሕ የተገኘባት፣ ፍትሐዊ ንጉሥ ባልነበረበት ዘመን ፍትሐዊ ንጉሥ የነገሰባት ሀገር ናት ነው ያሉኝ፡፡ ለዓመታት የነብዩ መሐመድ (ሰ.ወ.ዐ) መልእከተኞችን በሰላም እንዲኖሩ አደረጉ፡፡ ሰላም በኾነ ጊዜም ነብዩ ወዳሉባት ምድር ሄዱ፡፡ ከዚያ ዘመን ጀምሮ ታሪክ የሚቆጠርለት፣ በንጉሡ በነጋሲ ስም የተሰየመው አልነጃሽ መስጂድ በኢትዮጵያ አለ፡፡ ይህም ሥፍራ በሙስሊሙ ማኅበረሰብ የታወቀ ሥፍራ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ታላቅነት እና ፍትሐዊነት የሚመሰከርበት፣ ታሪክና ሃይማኖት የሚሰበክበት ሥፍራ ነው ነጃሺ መስጂድ፡፡

ነጃሺ ታላቅ ታሪክ የሚነገርበት ቢኾንም ብዙዎች እንዲያዩት እና የቱሪዝም መዳረሻ እንዲኾን ለማድረግ ግን በታሪኩ ልክ አልተሠራም ነው ያሉኝ ዑዝታዝ ባሕሩ፡፡ ታሪክን በማስታወስ፣ ኢትዮጵያ ባለውለታ እንደኾነች ለዓለም ማስተዋወቅ ይገባልም ብለዋል፡፡ ቅዱስ ቁርዓን በምድር ላይ ሂዱና የባለፈው ሕዝቦች የደረሱበትን ታሪክ ተመልከቱ ይላል፡፡ ቱሪዝምም ይሄን ያበረታታል፡፡ ታሪካዊ ሥፍራ ነውና ታሪክን ማስታወስ፣ እንዲህም ነበር እያሉ መናገር ይገባል ነው ያሉት፡፡ ታሪክን ማወቅም ለትውልድ ጠቃሚ ነውና፡፡

ነጃሺ የበዛ ታሪክ የሚነገርበት፣ ፍትሕ ባልነበረበት ጊዜ ፍትሕ የተገኘበት፣ የነብዩ መሐመድ መልእክተኞች በሰላምና በፍቅር የኖሩበት ታላቅ ሥፍራ ነው፡፡ እንኳን ለኢድ አል አደሃ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፡፡

በታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ አምራች ዘርፉን በማነቃቃት ትልቅ ሚና ነበረው” የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር
Next article“እንኳን ለዒድ አል አድሃ በዓል አደረሳችሁ!” ርእሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር)