“ኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ አምራች ዘርፉን በማነቃቃት ትልቅ ሚና ነበረው” የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር

94

አዲስ አበባ: ሰኔ 20/2015 ዓ.ም (አሚኮ) “በተኪ ምርቶች 2 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ማስቀረት ሲቻል 311 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ደግሞ በወጭ ንግድ ተገኝቷል” ብሏል የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር። እንደ ሀገር የተዳከመውን የአምራቹን ዘርፍ ለማነቃቃት የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ 3 ዓላማዎችን ይዞ ተነስቷል ነው የተባለው። ተኪ ምርቶችን ማምረት፣ የሥራ እድል ፈጠራ እና የውጭ ምንዛሬን ማስገኘት ከዓላማዎቹ መካከል እንደሚገኙበትም ተገልጿል።

ከሰሞኑ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች በሥራ ላይ ያሉ አምራች ተቋማትን ተመልክቷል። የጉብኝቱን ማጠቃለያ በማስመልከት ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ የሰጡት የኢፌዴሪ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስትር መላኩ አለበል ኢትዮጵያ ታምርት ከዓላማው አኳያ ጥሩ ውጤት የተገኘበት ነው ብለዋል።

የሀገር ውስጥ ጦርነት፣ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ፣ የራሽያ ዩክሬን ጦርነትና መሰል ችግሮች ያዳከሙት የሀገር ውስጥ አምራች ተቋም እንዲነቃቃ 434 ቢሊዮን ብር ብድር ተመቻችቶ ተሠርቷል ተብሏል። በዚህ ንቅናቄም በአማካይ 46 በመቶ የነበረው የአምራች ተቋማት አቅም አሁን ላይ 53 በመቶ መድረስ ችሏል ብለዋል ሚኒስትሩ። ከዚህ ባሻገር ንቅናቄው በተኪ ምርቶች 2 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ሲያስቀር 311 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ደግሞ በወጭ ንግድ አስገኝቷል ተብሏል። አሁን ላይም በውጭ ምንዛሬ፣ በሰው ኀይልና በጥሬ እቃ አቅርቦት ለሚታዩ ችግሮችም ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሠራም ተገልጿል።

ዘጋቢ፡- እንዳልካቸው አባቡ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ልዩነት የግጭት ምክንያት አይደለም” የዚህ ዓመት የአረፋ በዓል አሰጋጅ ሸክ የሱፍ ቢን ሙሐመድ ቢን ሰዒድ
Next article“ታላቅ ታሪክ ያለበት፣ መልእክተኞች ያረፉበት”