
👉የዘንድሮውን የሐጂ ሥርዓት ከ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ አማኞች እየታደሙበት ነው።
ባሕር ዳር: ሰኔ 20/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የኢድ አል አድሃ አረፋ በዓል በመላው ዓለም ሙስሊሞች ዘንድ በተለያዩ ዝግጅቶች በቅድስቲቷ ከተማ መካ እየተከበረ ነው፡፡ ከ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ አማኞች እየታደሙበት ነው በተባለው የዘንድሮው የሐጂ ሥርዓት ላይም ከመላው ዓለም የተውጣጡ ሙስሊሞች በመካ ከትመዋል፡፡
አደም እና ሐዋ ለመጀመሪያ ጊዜ በምድር ላይ እንደተገናኙበት የሚነገርለት እና ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) የመጨረሻ የሐጂ ሥርዓት ንግግር አድርገውበታል በሚባልለት ቅዱሱ የአረፋ ተራራ አናት ላይ ዛሬ በሺህዎች የሚቆጠሩ አማኞች የመድረስን እድል አግኝተዋል፡፡
አማኞቹ ቀኑን ሙሉ በጸሎት እና በስግደት በሚያሳልፉበት በዚህ ቀን የዚህ ዓመት የአረፋ በዓል አሰጋጅ ሸክ የሱፍ ቢን ሙሐመድ ቢን ሰዒድ “ልዩነት የግጭት ምክንያት አይደለም” ለዚህ ማሳያው ዛሬ በተቀደሰው የአረፋ ተራራ የታደመው የዓለም ኢስላም በቂ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡ዛሬ ማክሰኞ በአረፋ ተራራ ላይ የተሰጠውን ሃይማኖታዊ ትምህርት እና ስግደት የመሩት ሸክ የሱፍ ቢን ሙሐመድ የዓለም ሙስሊሞች በንግግር፣ በጸሎት እና በመልካም ተግባር ልንተባበር እና ግጭትን ልናስወግድ ይገባል ነው ያሉት፡፡
በዘንድሮው የሐጂ ሥርዓት ላይ አሰጋጅ እና ሰባኪ ኾነው ከመመረጣቸው በፊት በሳዑዲ አረቢያ በርካታ ከፍተኛ ሃይማኖታዊ ቦታዎች ላይ በመሪነት ያገለገሉት ሸክ የሱፍ ቢን ሙሐመድ ቢን ሰዒድ በነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) የተላለፈውን ሀዲስ በመጥቀስ ዘረኝነት በእስልምና ውስጥ ምንም መሰረት እንደሌለው ዓለም ሊያውቅ ይገባል ብለዋል፡፡ “በአሏህ ዘንድ ዓረብ በኾኑት እና ዓረብ ባልኾኑት መካከል፤ ነጭ ቆዳ ባላቸው እና ጥቁር ቆዳ ባላቸው መካከል ምንም ዓይነት ልዩነት የለም” ሲሉም የዓለም ኢስላም ዘረኝነትን እንዲጸየፍ ከፍ ባለው ተራራ ላይ ታላቅ የኾነውን አስተምህሮ አድርሰዋል፡፡
“አሏህ በመካከላችሁ የሚኖርን ደም መፋሰስ፣ የሌላን ሃቅ መመኘትን እና የሰውን ልጅ ክብር ዝቅ ማድረግን ከልክሏል” ያሉት ሸክ የሱፍ ቢን ሙሐመድ የቋንቋ፣ የቆዳ ቀለም እና የብሔር ልዩነት የግጭት መንስዔ የሚኾንበት ዘመን ማብቃት አለበት ብለዋል፡፡ ለፈጣሪ ያለን መገዛት ሌሎችን በማክበር፣ በመውደድ እና አንድ በመኾን ሲገለጽ፤ ጥላቻ እና ልዩነት ከአሏህ ወገን አይደሉም ሲሉም ተደምጠዋል፡፡
በአረብኛ ቋንቋ እየተላለፈ ያለው የዘንድሮው የአረፋ በዓል ሃይማኖታዊ ሥርዓት በ20 ቋንቋዎች እየተተረጎመ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ የዓለም ሕዝብ ዐይን እና ጆሮ እየደረሰ ነው ሲል የዘገበው ዘ ሚድል ኢስት ነው፡፡
በታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!