“ሐጂ ማድረግ፡- ምድራዊዋን እና የመጀመሪያዋን የፈጣሪ ቤት መጎብኘት ነው” ሼህ አብዱራሂም ሙሳ

108

ባሕር ዳር: ሰኔ 20/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ስፍር ቁጥር የሌለው የሰው ዘር ሁሉ ያለምንም ልዩነት ከሚሰባሰብባቸው ሃይማኖታዊ በዓላት መካከል አንዱ የሐጂ ሥርዓት ነው፡፡ አንድ ወቅት ምድረ በዳ የነበረችው ቅድስቲቷ ምድር መካ የአሏህ ክብር እና ፍቅር ተገልጦባት ሁልጊዜም በየዓመቱ በሚሊዮን በሚቆጠሩ የሃይማኖቱ ተከታዮች ዘንድ ትጎበኛለች፡፡ እንደ አዕዋፋት ሰማዩን ከሰው በላይ ከፍ ብለው እየቃኙ በሚያስመለክቱን የካሜራ ምስሎች ካዕባን የከበባት የበረዶ ክምር እንጂ የሰው ዘር አይመስልም ነበር፡፡

ነብዩ ኢብራሂም ልጃቸውን ኢስማኤልን እና ሃጀርን ይዘው ያደረጉትን የበርሃ ጉዞ 632 ዓ.ሂ ላይ ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ዳግም ተጓዙት፡፡ የሐጂ ሥርዓት በዚህ መልኩ ተጀመረ፡፡ በአረፋ በዓል የሐጂ ሥርዓትን ለመፈጸም ወደ ቅድስቲቱ ምድር መካ የሚጓዙ የሃይማኖቱ ተከታዮች በቆይታቸው የተለያዩ ቦታዎችን ይጎበኛሉ፡፡ ከመካ ወደ መዲና፣ ከአረፋ ወደ ሙዝደሊፋ፣ ከሚና ወደ ጀማረፋት፣ ከሚና ወደ መካ እየው ምቀኛ ምሥጋና ያቀርባሉ፡፡

የዘር ሐረግ፣ የቆዳ ቀለም፣ ምጣኔ ሃብታዊ ደረጃ፣ የመደብ ልዩነት እና ሥልጣን ሳይገድባቸው በአሏህ ፊት እኩል የሚኾኑበት ሥርዓት ነው- የሐጂ ሥርዓት፡፡

ከሁሉም የዓለም ክፍሎች የተሰባሰቡ ሙስሊሞች በዚያች ቅድስት ከተማ ከቅዱስ ተግባራት እና ምሥጋና ውጭ ከአፋቸው እንኳን ክፉ አይወጣም፡፡ ያሰባሰባቸው የአሏህ እዝነት እና ርህራሄ ነውና “አንተ ትብስ ፣ አንቺ ትብሽ” ከመባባል ያለፈ ክፉ ነገር ፈጽሞ የለም፡፡

በሚሊዮን የሚቆጠሩ አማኞች በሚሰባሰቡባት በዚያች ጠባብ የካዕባ ሥፍራ ለሶላት እንኳን በአንድ ጥሪ ብቻ ቦታ ቦታቸውን ይዘው ለስግደት ይዘጋጃሉ፡፡

በአረፋ በዓል ከሚፈጸሙ ሐይማኖታዊ ሥርዓቶች መካከል አንዱ ሐጂ ማድረግ ነው፡፡ የሐጂ ሥርዓት ሃይማኖታዊ ምክንያቱ ምንድን ነው? ስንል የሐጀጁ አንድ የሃይማኖቱን አስተማሪ አነጋግረናል፡፡ ሐጂ ማድረግ የእስልምና ሃይማኖት ከቆመባቸው አምስት ምሰሶዎች መካከል አንዱ ነው ያሉን ሼክ አብዱራሂም ሙሳ ናቸው፡፡ አንድ ሙስሊም በሕይዎት ዘመኑ ሊያሳካቸው ከሚፈልጋቸው ሃይማኖታዊ ምኞቶች መካከል ሃጂ ማድረግ ቀዳሚው ነው ይላሉ፡፡

ለመጀመሪያ ጊዜ ሐጂ ሳደርግ የተሰማኝን የደስታ ስሜት ያክል ደስታን አጣጥሜ አላውቅም የሚሉት ሼክ አብዱራሂም በቁራዓን የተማርናቸውን፣ በሃይማኖት አስተምህሮ መጻሕፍት ያነበብናቸውን እና ከታላላቆቻችን የሰማናቸውን ቅዱስ ቦታዎች መመልከት የተለየ ስሜት ይሰጣል ይላሉ፡፡ የሐጂ ሥርዓት ዓለም ስለእኩልነት ልትማርበት የሚያገባ ጠቃሚ እና ገንቢ እሴቶች ያሉት ነው የሚሉት ሼክ አብዱራሂም መከባበሩ፣ መቻቻሉ እና አንድነቱ ፍጹም የተለየ ስሜትን የሚሰጥ ነው ይላሉ፡፡

“ሐጂ ማድረግ በምድር ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገነባችውን የአሏህን ቤት መጎብኘት ነው” የሚሉት ሼክ አብዱራሂም ካዕባን ሰባት ጊዜ ሙሉ እየዞሩ ማመስገን ምን ዓይነት የደስታ ስሜት ይፈጥራል ብትለኝ መግለጽ ይከብዳል ይላሉ፡፡ ከነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ጉዞ በኋላ አካላዊ አቅማቸው፣ ጤንነታቸው እና የገንዘብ አቅሙ የፈቀደለት የሃይማኖቱ ተከታዮች ሁሉ በሕይዎት ዘመናቸው አንድ ጊዜ ሐጂ እንዲያደርጉ ያስገድዳልም ይላሉ፡፡

በመካ በሚገኘው ታላቁ መስጊድ እምብርት ላይ ያለው ጥቁር ሐር ለበስ ካዕባ በነቢዩ ኢብራሂም እና በልጃቸው እስማኤል የተገነባ ነው። በዚህ መስጂድ ዙሪያ ያለው የሐጃጆች ውበት እና ሙሃባ የተለየ ነው፡፡ ሐጂ የልዩነትን በር አጥብቦ የአንድነትን፣ የመተሳሰብን እና የአብሮነትን መንገድ የሚከፍት ነው የሚሉት ሼህ አብዱራሂም የሐጅ ዋና ዓላማውም አንድነትን ማጽናት ነው ብለዋል፡፡

የሐጅ አስተምህሮ ጠሊቅ፣ ሚስጥሩ ረቂቅ እና ፋይዳው ትልቅ ነው የሚሉት ሼክ አብዱራሂም እኛ የአሏህ እንግዶች ነን፤ የአሏህ እንግዶች ደግሞ የፈጣሪያቸውን ቤት መጎብኘታቸው ብዙ እንዲያተርፉ ይረዳቸዋል ብለዋል፡፡ እኔ በመሐጀጄ ብዙ ብዙ አትርፌያለሁ፤ ሌሎችም ያ ሙሃባ እንዲደርሳቸው እመኛለሁ ነው ያሉት፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleእንኳን ለታላቁ የዒድ አል አድሃ በዓል አደረሳችሁ!
Next article“ልዩነት የግጭት ምክንያት አይደለም” የዚህ ዓመት የአረፋ በዓል አሰጋጅ ሸክ የሱፍ ቢን ሙሐመድ ቢን ሰዒድ