
ባሕር ዳር: ሰኔ 20/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ዓለም አቀፉ የትምህርት ትብብር ድርጅት ያስቀመጣቸው ውጥኖች እውን እንዲሆኑ ኢትዮጵያ ቁርጠኛ መሆኗን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ፡፡
እየተካሄደ በሚገኘው ዓለም አቀፍ የትምህርት ትብብር ድርጅት ልዩ ጉባኤ የወቅቱ የጠቅላላ ጉባዔው ፕሬዚዳንት አቶ ደመቀ መኮንንድርጅቱ ያስቀመጣቸው ውጥኖች እውን እንዲሆኑ ኢትዮጵያ ቁርጠኛ መሆኗን ገልፀዋል፡፡
የባለ ብዙ ወገን ትብብር ቁልፍ ጕዳይ መሆኑን አስገንዝበዋል።
ትብብሩ በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት ድህነትን ጨምሮ እያጋጠሟቸው ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ትልቅ ሚና እንዳላቸውም አስገንዝበዋል፡፡
የዓለም አቀፉ የትምህርት ትብብር ድርጅት ዋና ፀሐፊ ሼክ መንሱር ቢን ሙሠላም÷ ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሣካት እና የማህበረ ኢኮኖሚ ልማትን ስኬታማ ለማድረግ ይቻል ዘንድ አባል ሀገራቱ የሚከተሏቸው የትምህርት አጋዥ ሚና እንዲኖረው ማስቻል ለመሠረታዊ ለውጥ አብይ ጉዳይ ነው ብለዋል።
ለዚህ ይረዳ ዘንድ በትምህርት ዘርፍ ላይ ያሉ ተመራማሪዎች፣ የዩኒቨርሲቲ ምሁራን፣ ወጣቶች የአባል ሀገራት መንግስታት የበኩላቸውን ድርሻ ሊወጡ ይገባል ነው ያሉት፡፡
ለዚህም የዓለም አቀፉ የትምህርት ትብብር ድርጅት አስፈላጊውን የገንዘብ፣ የቴክኒክና የቁሳቁስ ድጋፍ ያደርጋል ማለታቸውን የውጭ ጉይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡
አባል ሀገራቱ የሚከተሏቸው የትምህርት ሥርዓቶች ለጋራ ዕድገት አመቺ የሆነ ቅኝት እንዲኖራቸው ማድረግ ጠቃሚ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
ዓለም አቀፉ የትምህርት ትብብር ድርጅት (ኦኢሲ) ሚዛናዊ፣ አካታች እና ሁሉን አቀፍ የትምህርት ስርዓት በመዘርጋት በእኩልነት፣ ፍትሐዊነት እና አጋርነት ላይ የተመሰረተ ልማት ማምጣትን ያለመ ነው።
ጉባኤው ሁለት ቀናት በሚኒስትሮች ደረጃ የሚካሄድ ሲሆን በቀሪዎቹ ቀናት የድርጅቱ አባል አገራት መሪዎች ምክክር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!