
የቆላማ አካባቢዎች የኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት ዛሬ በአዲስ አበባ ይፋ መደረጉን የሠላም ሚኒስቴር አስታውቋል።
ባሕር ዳር፡ ሕዳር 25/2012ዓ.ም (አብመድ) የሠላም ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል ፕሮጀክቱን አስመልክቶ ሲናገሩ የኢትዮጵያ አርብቶና ከፊል አርብቶ አደር አካባቢዎች ሰፊ የቆዳ ሽፋን የሚዙና በተደጋጋሚ ድርቅ የሚያጠቃቸዉ መሆኑን ገልፀዉ መርሀ ግሩ የአርብቶ አደርና ከፊል አርሶ አደሩን ማኅበረሰብ ኑሮ ለማሻሻል ትልቅ ፋይዳ እንዳው አመልክተዋል።
የሠላም ሚኒስቴር አርብቶ አደሩንና ከፊል አርሶ አደሩን የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ ለማድርግ ሰፊ እንቅስቃሴዎችን ሲያደርግ መቆየቱን የገለፁት ወይዘሮ ሙፈሪያት በቀጣይ የአርብቶ አደሩንና የከፊል አርሶ አደሩን ማኅበረሰብ ተጠቃሚ ለማድረግ ሥራዎች ተጠናክረዉ እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል ።
ፕሮጀክቱ በሱማሌ፣ አፋር፣ ኦሮሚያ፣ ቤንሻንጉል፣ ጋምቤላና ደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልሎች የሚገኙ አርብቶና ከፊል አርሶ አደሮችን የሚሸፍን በ100 ወረዳዎች የሚተገበር ነው።
መርሀ ግብሩ ለ6 ዓመታት የሚቆይ 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሕዝብ ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑ ተመላክቷል።
የፕሮጀክቱ በጀት ከዓለም ባንክ ‹ግሩፕ›፣ ከዓለም አቀፍ ፈንድ ለግብርና እና ከለጋሽ ማኅበረሰብ የተገኘ 451 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ነዉ ተብሏል።
በአርብቶና በከፊል አርሶ አደሩ አካባቢዎች የተቀናጀ ልማት ማፋጠን፣ የእንስሳት እርባታን ማሻሻልና ገበያ ማስፋፋት፣ የመሠረተ ልማት አገልግሎቶችን ማዘመንና የሰዉ ኃይልን ማብቃት የፕሮጀክቱ ዋና ዋና የትኩረት መስኮች ናቸው።
ፕሮጀክቱ የአርብቶና ከፊል አርሶ አደር ማኅበረሰብን በቀጥታ በማሳተፍ ይከናወናል። ፕሮጀክቱ በሠላም ሚኒስቴር ስር የሚተዳደር ሆኖ ቀጥታ ተጠሪነቱ ለፌዴራሊዝምና የአርብቶ አደር ጉዳዮች ዘርፍ ነው ተብሏል።
የግብርና ሚኒስቴር፣ የሱማሌ፣ የአፋርና የጋምቤላ ክልል ርዕሳነ መስተዳድሮችና የኦሮሚያና የደቡቡ ክልል ተወካዮች እንዲሁም የለጋሽ ሀገራት ተወካዮች ተገኝቸዋል።