
ደብረ ታቦር : ሰኔ 20/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ችግኞችን ከመትከል ባለፈ እንዲጸድቁ ያለመ ሥራ እየሠራ መኾኑን ለዚህም አሠራር ማበጀቱን የደብረታቦር ከተማ አሥተዳደር ግብርና መምሪያ አስታውቋል።
የከተማው የከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች ስልጠና መጠናቀቅን ምክንያት በማድረግ ሰልጣኞችና በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ችግኝ ተክለዋል፡፡
የደብረታቦር ከተማ አሥተዳደር “ነገን ዛሬ እንትከል” በሚል መሪ መልዕክት የአረንጓዴ አሻራ 5ኛ ዓመት የችግኝ ተከላ መርኃ ግብርን በደብረታቦር ከተማ ጋፋት ትምህርት ቤት አስጀምሯል፡፡
በችግኝ ተከላው ሲሳተፉ ያገኘናቸው በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ደብረታቦር ከተማን ውብ እንድትኾን በሁሉም ረገድ እንደሚሠሩ ተናግረዋል፡፡
የደብረታቦር ከተማ አሥተዳደር ግብርና መምሪያ ኀላፊ ማርየ በለጠ (ዶ.ር) ዘንድሮ የሚተከሉ ችግኞች ጸድቀው አገልግሎት እንዲሰጡ ታልሞ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
የከተማው ብልጽግና ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ታደለ እሸቴ በበኩላቸው በክረምቱ ወራት በርካታ የበጎ ፈቃድ ሥራዎችን ለመሥራት ከወጣቶች ጋር የመግባባት ሥራ መሠራቱንና ሕዝቡም አጠናክሮ እንደሚሠራ ተናግረዋል፡፡
የደብረታቦር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ደሳለኝ በላቸው ለከተማው ውበትና ጽዳት ችግኝ መትከል ብቻ ሳይኾን ተንከባክቦ ማሳደግ እንደሚገባና ነዋሪዎችም በባለቤትነት እንዲያለሙ ከተማ አሥተዳደሩ ይሠራል ብለዋል።
በችግኝ ተከላ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል የገጠር መንገድ ኮንስትራክሽን ኤጀንሲ ዋና ሥራ አሥኪያጅ ቀለሙ ሙሉነህ በአየር ንብረት ለውጥ የሚመጣን ችግር ለመቋቋም የአረጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መፍትሄ መኾኑን ጠቅሰው በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው ሰፊ የችግኝ ተከላም ውጤታማ መኾኑን ተናግረዋል።
ዘጋቢ፡- ዋሴ ባየ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!