በሰሜን ወሎ ዞን የክረምት ወራት ለማከናወን የታሰበው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተጀመረ፡፡

52

ወልድያ: ሰኔ 20/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በሰሜን ወሎ ዞን በመጭዎቹ ክረምት ወራት የሚከናወነው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በራያ ቆቦ ወረዳ ጎብየ ቀበሌ ነው የተጀመረው፡፡

አገልግሎቱ የአቅመ ደካማ ቤቶችን ከመሥራትና ከማደስ በተጨማሪ በትምህርት ፣ በደም ልገሳ ፣በግብርና እና በጤና ዘርፎች ላይ ትኩረት ይደረጋል ተብሏል።

የሰሜን ወሎ ዞን ወጣትና ስፖርት ጉዳይ መምሪያ ኀላፊ አቶ ባንቴ ምሥጋናው በበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ከ330 ሺህ በላይ ወጣቶች እና ግለሰቦችን በማሳተፍ ከ9 መቶ ሺህ በላይ የኀብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ መታሰቡን ተናግረዋል።

በማስጀመሪያ መርኃ ግብሩ በጎብየ ቀበሌ አራት የገንዘብ አቅም የሌላቸው ወገኖች ቤት እድሳት ተደርጓል፡፡

ቤታቸው ከታደሰላቸው ወገኖች መካከል እማሆይ ያልጋ አጥያ ሲፈራርቅባቸው የነበረውን ዝናብና ፀሀይ እድሳቱ እንደሚያስቀርላቸው ተናግረው ለዚህም ምሥጋና አቅርበዋል።

የዞኑ አሥተዳዳሪ አቶ ጋሻው አስማሜ ዞኑ በጦርነትና መሰል ምክንያቶች ጉዳት ከማስተናገዱ ጋር ተያይዞ የሌሎችን ድጋፍ የሚሹ ወገኖች መኖራቸውን ገልጸዋል፡፡

በተለይ በትምህርት መርጃ ቁሳቁስና በምግብ እጥረት ምክንያት ከትምህርት ገበታ ያቋረጡ በርካታ ተማሪዎች መኖራቸውን የተናገሩት አቶ ጋሻው እነዚህን ህጻናት ወደ ትምህርት ገበታ ለመመለስ የኹሉንም ድጋፍ የሚሹ መኾኑን ገልጸው የሰሜን ወሎና አካባቢው ተወላጆች እና ወዳጆች የትምህርት ቁሳቁስና ገንዘብ በማሰባሰብ ወገናዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ባለ ዓለምየ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article”የዒድ አል አድሃ አረፋ በዓልን ስናከብር አቅመ ደካሞችን በማገዝና ለሰላም ዘብ በመቆም ሊኾን ይገባል” የደብረ ማርቆስ ከተማ መስጂድ ኢማም ሼህ መሐመድ ሽፋው
Next articleችግኞችን ከመትከል ባለፈ እንዲጸድቁ ያለመ ሥራ እየሠራ መኾኑን የደብረታቦር ከተማ አሥተዳደር ገለጸ፡፡