
ደብረ ማርቆስ: ሰኔ 20/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የዒድ አል አድሃ አረፋ በዓል ነብዩ ኢብራሒም የአላህ (ሰ.ዐ) ትዕዛዝን ለመፈጸም በፍጹም ትህትናና ታዛዥነት ልጃቸው እስማኤልን ለመስዋዕትነት ያቀረቡበት በዓል ነው፡፡ አሏህ (ሰ.ዐ) የነብዩ ኢብራሂም መታዘዝን ተመልክቶ በምትኩ በግ እንዳቀረበለትም የእምነቱ አስተምህሮ ያስረዳል፡፡
እንደሌሎች በዓላት ኹሉ ድሆችና አቅመ ደካሞች በሚታሰቡበት በዚሁ የዒድ አል አድሃ አረፋ በዓል ለመስዋዕትነት ከቀረበው ማካፈል እንደ ግዴታ ይቀመጣል። ይህም ደስታን የጋራ የማድረግ ኃይል እንዳለው በደብረ ማርቆስ ከተማ ከሚገኙ የእምነቱ ተከታዮች መካከል ሼህ ወለላው ሰይድና ነህያን የሱፍ ተናግረዋል፡፡
የዒድ አል አድሃ አረፋ በዓልን ስናከብር አንድነታችንን በማጠናከር ከምንም በላይ ደግሞ የእስልምና መሰረት የኾነው ሰላምን በመጠበቅና ሰላምን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ውስጥ የበኩላችንን በመወጣት ሊኾን ይገባልም ብለዋል የእምነቱ ተከታዮች፡፡
ሕዝበ ሙስሊሙ አቅመ ደካሞችን በመርዳትና ከጎናቸው በመቆም በዓሉን ሊያከብር ይገባል ያሉት ደግሞ የደብረ ማርቆስ ከተማ መስጂድ ኢማም ሼህ መሀመድ ሽፋው ናቸው፡፡ ያለ ሰላም ወጥቶ መግባት፣ በሀዘንም በደስታም ለመገናኘት አይቻልምና ሕዝበ ሙስሊሙ ለሰላም ዋጋ ትልቅ ቦታ በመስጠት ሰላሙንና አንድነቱን ሊያጸና ይገባልም ብለዋል።
ሼህ መሀመድ በመልዕክታቸው ሀገራችን ያለችበትን ኹኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት የተፈናቀሉ ወገኖችን ማሰብና መደጋገፉ ተጠናክሮ መቀጠል አለበትም ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- መልሰው ቸርነት
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!