
ፍኖተ ሰላም: ሰኔ 20/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የምዕራብ ጎጃም ዞን ግብርና መምሪያ የዘንድሮው የክረምት አረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርኃ ግብርን በፍኖተ ሰላም ከተማ አሥተዳደር ሸምበቁማ የደፋስ ቀበሌ አስጀምሯል።
በመርኃ ግብሩ ከዞኑ ሁሉም ወረዳዎችና ከተማ አሥተዳደሮች የተውጣጡ መካከለኛና ከፍተኛ አመራሮች ተሳትፈዋል።
የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብሩን ያስጀመሩት የዞኑ ዋና አሥተዳዳሪ አቶ መልካሙ ተሾመ ባለፉት ዓመታት በተከናወነው የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርኃ ግብር የተገኙ ልምዶችን በመውሰድ በዚህ ዓመት ለስኬታማነቱ ሁሉም አካል ርብርብ ሊያደርግ ይገባል ብለዋል።
የሚተከሉ ችግኞችም የደን ሽፋንን ከማሳደግ ባሻገር የማኀበረሰቡን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ እንዲኾኑ መሥራት እንደሚገባውም አስገንዝበዋል።
ችግኞችን መትከል ብቻውን ግብ አይደለም ያሉት ዋና አሥተዳዳሪው ችግኞች ተተክለው አስኪጸድቁ ድረስ ጥበቃና እንክብካቤ እንዲደረግላቸው አሳስበዋል።
የምዕራብ ጎጃም ዞን ግብርና መምሪያ ኀላፊና ምክትል አሥተዳዳሪ አቶ ጥላሁን አለምነህ በዚህ ዓመት ለአረንጓዴ አሻራ ብቻ 202 ሚሊዮን የደንና 4 ሚሊዮን የፍራፍሬ ችግኝ ለተከላ ተዘጋጅቷል ብለዋል።
እንዲሁም በቀጣይ በአንድ ጀምበር ብቻ 30 ሚሊዮን የሚጠጋ ችግኝ ለመትከል ዕቅድ መያዙን ነው የተናገሩት። ዛሬ በይፋ የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርኃ ግብርም ለቀጣይ አንድ ወር ጊዜ በዞኑ በ22ቱ ወረዳዎችና ከተማ አሥተዳደሮች በንቅናቄ የሚካሄድ ነው ብለዋል።
የፍኖተ ሰላም ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ልየው አንሙት በበኩላቸው በዚህ ዓመት የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር በ21 ሄክታር መሬት ላይ ከ236 ሺህ በላይ የደንና ከ40 ሺህ በላይ የፍራፍሬ ችግኞችን ለመትከል ዕቅድ ተይዞ ወደ ተግባር መገባቱን ተናግረዋል።
ዛሬ ላይ የማስጀመሪያ መርኃ ግብር የተካሄደበት የሸምበቁማ የደፋስ ቀበሌ ግማሽ ሄክታር የተራቆተ መሬት ሲኾን አካባቢው ለከተማው ውኃ መገኛ በመኾኑ ችግኝ መተከሉ ብዝኃ ህይዎቱ እንዲጠበቅ ያደርገዋል ብለዋል።
በችግኝ ተከላው ሲሳተፉ ያገኘናቸው የሰሜን አቸፈር ወረዳ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ማንአህሎት አዲስ እና የጎንጂ ቆለላ ወረዳ ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት አደረጃጀት ዘርፍ ኀላፊ ሃይማኖት ድረስ በዞኑ የአረንጓዴ አሻራ ማስጀመሪያ ንቅናቄ ተገኝተው አሻራቸውን በማኖራቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል፡፡ በቀጣይ በየወረዳዎቻቸው የችግኝ ተከላ መርኃ ግብሩን ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጁ መኾናቸውን ተናግረዋል።
ዘጋቢ፡- ዘመኑ ይርጋ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!