
ባሕር ዳር: ሰኔ 20/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮ ቴሌ ኮም የሰሜን ሰሜን ምዕራብ ሪጅን ኦፕሬሽን ማናጀር አቶ ወርቃአለማው ዳኛቸው ለሶስቱ ጎንደር ዞኖች የተለያዩ የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
ግምቱ ግማሽ ሚሊዮን ብር የሚያወጣ የትምህርት ቁሳቁስ ነው ድጋፍ የተደረገው።
ድጋፉ ወንበርና ጠረጴዛን ያካተተ ሲኾን ማናጀሩ ለሰሜን፣ ደቡብና ማዕከላዊ ጎንደር ዞን የተመረጡ ትምህርት ቤቶችና ለአንድ በጎ አድራጎት ማኅበር የተደረገ መኾኑን ገልጸዋል።
የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ትምህርት መምሪያ ኅላፊ አቶ ክንዱ ዘውዱ በበኩላቸው በዞኑ የሚገኙ ከደረጃ በታች የሆኑ ትምህርት ቤቶችን ገፅታ ለመቀየር ጥረቶች እየተደረጉ ነው ብለዋል።
በተለይም በግብዓት ላይ የሚታየውን ችግር ለማስተካከል መንግሥት ከሚያደርገው ጥረት ባለፈ የተለያዩ ተቋማትና ግለሰቦች ግብዓት በማሟላት በኩል ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ መሆኑን ኅላፊው ገልጸዋል።
ኢትዮ ቴሌኮም ላደረገው ድጋፍ ምስጋና ያቀረቡት ኅላፊው ሌሎች ተቋማትም ለትምህርት ዘርፉ ችግሮች መስተካከል የበኩላቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።
ድጋፍ የተደረገላቸው የትምህርት ቤት ተወካዮች በሰጡት አስተያየት እንደገለጹት ኢትዮ ቴሌኮም ለትምህርት ቅድሚያ ሰጥቶ ላደረገው የቁሳቁስ ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።
በቀጣይም ተቋሙ ማኅበራዊ ኅላፊነቱን እየተወጣ እንደሚቀጥል አቶ ወርቃለማው ገልጸዋል። ዘገባው የማዕከላዊ ጎንደር ዞን መንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ነው።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!