
አዲስ አበባ: ሰኔ 20/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ የሰላም ልኬት የሙከራ ጥናት ውጤት ይፋ ተደርጓል። ለሌሎች ጥናቶችና የሰላም ግንባታ ሥራዎች እንደ ግብዓት የሚውል እንደኾነም ተገልጿል፡፡
የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ብናልፍ አንዷለም ጥናቱን በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ለማድረግ የታሰበው ከ 3 ዓመት በፊት እንደነበር ገልጸው ከኮረና ወረርሽኝ ጀምሮ በሀገሪቱ ባጋጠሙ የተለያዩ ሰው ሠራሽና ተፈጥሯዊ ችግሮች ምክንያት በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በነበረው አለመረጋጋት ሥራውን በሚፈለገው ጊዜ በሁሉም ክልሎችና ከተማ አሥተዳደሮች ማከናወን አልተቻለም ብለዋል።
የኢትዮጵያ የሰላም ልኬት ሥራ ከዚህ በፊት በዚህ መልኩ ያልተሠራና ጥናቱ ከግጭት ትንተና ይልቅ አዎንታዊ ሰላም እና ማኅበራዊ እሴቶች ላይ በማተኮር የተሠራ መኾኑን አቶ ብናልፍ ገልጸዋል።
ጥናቱ እንደመነሻ ያገለግላል ያሉት ሚኒስትሩ መሥሪያ ቤቱ ዕቅዶቹንና ትግበራዎቹን እንዲፈትሽ አስችሎታል ነው ያሉት፡፡ ብሔራዊ የዘላቂ ሰላም ግንባታ ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን ለማውጣት አበርክቶ እንደሚኖረውም አስገንዝበዋል።
የሙከራ ጥናቱ በሦስት ክልሎች በሰላም እና አብሮነት ዙሪያ ሊጠናከሩ የሚችሉ እና በቀጣይ ሊሠራባቸው የሚገቡ ክፍተቶችን ያሳየ ነው። ከሁሉም በላይ ጥናቱን በመላ ሀገሪቱ በአጠረ ጊዜ ለማካሄድ በቂ ልምድና አቅም እንደተፈጠረም አቶ ብናልፍ ተናግረዋል።
ጥናቱ በሲዳማ፣ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እንዲሁም በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝብ ክልሎች የተደረገ ሲኾን በግለሰብ፣ በቤተሰብ፣በማኅበረሰብ እና በአጎራባች አካባቢዎች ደረጃ ተመስርቶ የተሠራ ጥናት መኾኑ ተገልጿል።
በጥናቱ እንደተመላከተው ከግለሰብ ወደ ቤተሰብ፣ ማኅበረሰብና አጎራባች አካባቢዎች የሰላም ሁኔታው እየቀነሰ እንደመጣ ግኝቱ ያሳያል።
ዘጋቢ፡- ድልነሳ መንግሥቴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!