የድኅረ ምርት ብክነትን ለመቀነስ እየተሠራ መሆኑን አርሶ አደሮችና የግብርና ባለሙያዎች ገለጹ፡፡

670

ባሕር ዳር፡ ሕዳር 25/2012ዓ.ም (አብመድ) የዓለም የምግብ ድርጅት በኢትዮጵያ የሚታየው የድህረ ምርት የምግብ እህል ብክነት አሳሳቢ እንደሆነ አስታወቀ።

የዓለማችን ጥንቃቄ የጎደለው የምግብ እህል አያያዝ በየዓመቱ 100 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ ያሳጣል ነው የተባለው፡፡

የዓለማችን ሕዝብ የምግብ እህል አጠቃቀም ትኩረት የተነፈገው መሆኑ ይነገራል። ከድህረ-ምርት አያያዝ እስከ አጠቃቀም ባሉት ሂደቶች ውስጥ በምግብ እህል ላይ የሚታየው ብክነት ከፍተኛ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ። የዓለም የምግብ ድርጅት (ፋኦ )በቅርቡ እንዳስታወቀው ከዓለም ሕዝብ ዓመታዊ ፍጆታ መካከል 1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ቶን ያክሉ ለብክነት ይዳረጋል። ይህም ከአጠቃላይ ዓመታዊ ምርቱ ሲሶ ያህሉን ይይዛል። ብክነቱ 990 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ያክል ኪሳራ እንደሚያደርስም ነው መረጃው የሚያሳየው።

በኢትዮጵያም የግብርና ምርቶች ላይ በየዓመቱ የሚከሰተው ብክነትም አሳሳቢ ነው ተብሏል። ከአጠቃላይ ምርቱ ከ20 እስከ 30 በመቶ ለብክነት ሊዳረግ እንደሚችል ጥናቶች ያሳያሉ። ብክነቱ በአብዛኛው በድህረ ምርት አሰባሰብ ጊዜያት በሚከናወኑ ጥንቃቄ የጎደላቸው አሠራሮች ምክንያት እንደሆነ በምሥራቅ ጎጃም ዞን ያነጋገርናቸው አርሶ አደሮች ይናገራሉ። የምሥራቅ ጎጃም ዞን ደብረ ኤልያስ ወረዳ ጓይ ቀበሌ ነዋሪው አርሶ አደር አቶ ወርቁ ጌታነህ ለአብመድ እንደተናገሩት እርሳቸውን ጨምሮ ሌሎች የአካባቢው አርሶ አደሮች የምርት ብክነቶችን ለመከላከል የሚያደርጉት ጥረት ዝቅተኛ ነው።

በአጨዳ፣ ውቂያ፣ ወደ ቤት በሚያጓጉዙበት ወቅት እንዲሁም በእህል ጉድጓድ፣ በጎተራ ሲያከማቹ ለብክነት የሚዳረግ መሆኑን አርሶ አደሩ ነግረውናል። ከነቀዝና ከተለያዩ ነብሳት ለመከላከል የሚከናወነው የኬሚካል ርጭትና ማሸትም በጤናቸው ላይ ጉዳት እንዳለው ግንዛቤ እንዳላቸው አስረድተዋል። ይሁን እንጅ ‹‹ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ብክነቱ በኢኮኖሚ ላይ እያደረሰው ስላለው ሁኔታ የአርሶ አደሩ ግንዛቤ እያደገ ይገኛል›› ብለዋል።

በአጨዳ ወቅት የሚደርሰውን ብክነት ለመቀነስ ከ4 ሄክታር በላይ የስንዴ ሰብላቸውን በኮምባይነር ለመሰብሰብ እና እስከ ቤታቸው ድርስ በመኪና ለመውሰድ በዝግጅት ላይም ናቸው። በምርት ዘመኑ ለማግኘት ያሰቡትን 150 ኩንታል የተለያዩ ምርቶችም በዘመናዊ የብረት ጎተራ ለማከማቸት ቅድመ ዝግጅት እያደረጉ ነው። ሦስት የብረት ጎተራዎችን መግዛታቸውንም አረጋግጠናል።

የደብረ ኤልያስ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት እንዳስታወቀው ከእርሻ እስከ ጉርሻ ድረስ የሚታየውን የምግብ እህል ብክነት ለመከላከል በሁሉም የወረዳው አካባቢዎች ለሚገኙ አርሶ አደሮች ግንዛቤ ተፈጥሯል። ከዚህ በፊት የነበረውን ባሕላዊ የሰብል አሰባሰብ በዘመናዊ ለመተካት አርሶ አደሩ በኮምባይነር የማጨድ ልምዱን እያሰፋ እንደሚገኝ የጽሕፈት ቤቱ ሰብል ልማት ቡድን መሪ አቶ መሃሪ ፀጋየ አስረድተዋል።

አርሶ አደሩን መሠረት አድርገው የብረት እህል ማከማቻዎችን እያመረቱ የሚያቀርቡ አራት ኢንተርፕራይዞች በሥራ ላይ ይገኛሉ። ይህ መረጃ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ 315 የብረት ጎተራዎች ለአርሶ አደሮች መሠራጨታቸውንም ጠቁመዋል። ከ6 ሺህ 876 በላይ ዘመናዊ “ፒክስ” ከረጢት እንደተሠራጨም ተገልጿል።

በድህረ ምርት ወቅት የሚከሰተውን ብክነት ለመቀነስ እየተደረገ ካለው እንቅስቃሴ ጎን ለጎን ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በምርት ላይ ሊያስከትለው የሚችለውን ጉዳት ለመከላከል የክልሉ ግብርና ቢሮ እየሠራ መሆኑን መዘገባችንም ይታወቃል። የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ማብቂያ ለማሳካት ይፋ አድርጎት የነበረው ዕቅድ እንደሚያሳየው ደግሞ በሀገሪቱ የሚስተዋለውን የምርት ብክነት ከ50 በመቶ በላይ ለመቀነስ የሚያስችል አሠራር ተግባራዊ እየተደረገ ነው፡፡

ዘጋቢ:- ኃይሉ ማሞ

Previous articleሙስናና ብልሹ አሠራር የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችን ተሳትፎ የሚጠይቅ ቢሆንም አመራሮች በሌሎች አጀንዳዎች ተጠምደው ለጉዳዩ ትኩረት አልሰጡትም ተባለ፡፡
Next articleየጥምቀት በዓልን በጎንደር ከተማ በድምቀት ለማክበር በሰፊው ዝግጅት እየተደረገ ነው።