“የአረፋን በዓል ከቤታቸው፣ ከንብረታቸው እና ከቀያቸው ከተፈናቀሉ ወገኖች ጎን ኾነን በአብሮነት እና በደስታ እናሳልፍ” ሼህ ሙሐመድ አንዋር

29

ባሕር ዳር: ሰኔ 20/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት 1444ኛው ዓመተ ሂጅራ ዒድ አል ዓድሃ አረፋ በዓልን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል። መግለጫውን የሰጡት የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት ሼህ ሙሐመድ አንዋር እና የከፍተኛ ምክር ቤቱ ዋና ጸኃፊ ሼህ አብዱራህማን ሱልጣን ናቸው።

ምክትል ፕሬዝዳንቱ ሼህ ሙሐመድ አንዋር “በዚህ ወደ አምላካችን በምንቃረብበት በዓል ከቤታቸው፣ ከንብረታቸው እና ከቀያቸው ከተፈናቀሉ ወገኖች ጎን ኾነን በአብሮነት እና በደስታ እንድናሳልፍ አደራ እላለሁ” ብለዋል። በዓሉ ቀድሞ በነበረው ኢትዮጵያዊ ስሜት እና አብሮነት ከወገኖቻችን ጋር ተደስተን እና ተጫውተን የምንውልበት በዓል መኾን አለበት ሲሉም በመግለጫቸው አንስተዋል። አንድነት እና መተዛዘን የሁሉም ሙስሊሞች ልምድና ተግባር ኾኖ እንዲቀጥልም አሳስበዋል።

ሁሉም ሙስሊም ማኅበረሰብ ከዒድ ሶላት በኃላ የሚቀርበውን እርድ ለቤተሰብ፣ ለወገኖቻችን እና ለተቸገሩት ሁሉ በማከፋፈል ሃይማኖታዊ ትዕዛዙን መፈጸም አለበት ብለዋል። በዚህ መልኩ ማኅበራዊ ግንኙነትን የበለጠ ማጠናከር እንደሚያስፈልግም በመግለጫቸው ጠቁመዋል።

የምክር ቤቱ ዋና ጸኃፊ ሼህ አብዱራህማን ሱልጣን በበኩላቸው ነቢዩ መሐመድ(ሰ.ዐ.ወ) በመጨረሻው የአረፋ መልዕክታቸው “ሰዎች ኾይ ደማችሁ እና ክብራችሁ በእናንተ ላይ እርም ነው፣ አደራ የተቀመጠበት አደራውን ይወጣ፣ መበዳደልም የለም” እንዳሉት ሁሉ በዓሉ አንድነታችንን የምናጠናክርበት እና ከመጥፎ ነገሮች የምንርቅበት መኾን አለበት ብለዋል። “በሴቶቻችሁ ላይ መብት እንዳላችሁ ሁሉ ሴቶቻችሁም በእናንተ ላይ መብት አላቸው፤ ሙዕሚኖች ወንድማማቾች ናቸው፣ አንድም ሰው የወንድሙን ገንዘብ ያለፈቃድ መውሰድ ክልክል ነው” የሚለው መልዕክትም ነቢዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) በዚሁ ታላቅ ቀን ያስተላለፉት መልዕክት ነበር ብለዋል። ስለዚህ ራሳችንን ከመጥፎ ነገሮች ሁሉ በማቀብ እና የማንንም መብት ሳንጋፋ በዓሉን ማክበር ይገባናል ሲሉም ዋና ጸኃፊው መልዕክት አስተላልፈዋል።

ሼህ አብዱራህማን የአረፋ በዓልን ስናከብርም ሃይማኖቱ በሚያዝዘው መሰረት የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳት መኾን አለበት ብለዋል። በተለይም የተፈናቀሉ ወገኖችን በአረፋ ዕርድ እና በመሰል የሰደቃ ዓይነቶች ማሰብ አለብን ሲሉም አሳስበዋል። ከሌሎች እምነት ተከታይ ወገኖቻችን ጋርም እንደተለመደው በሰላማዊ እና በመተሳሰብ እንዲሁም በመከባበር በዓሉን እናሳልፍ ብለዋል በመግለጫው።

ሁሉም ሙስሊም ማኅበረሰብ ለሀገሩ እና ለክልሉ ዘላቂ ልማት የሚጠበቅበትን ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርግም ጥሪ አቅርበዋል። በመጨረሻም “ዒዳችን ሥነ ሥርዓት፣ መተናነስ፣ መከባበር፣ መቻቻል እና እኩልነት የሰፈነበት የሰላም ፣ የፍቅር፣ የአንድነት እና የአሏህ ራሕመት እዝነት የሚወርድበት እንዲኾንልን ልባዊ ምኞታችንን እንገልጻለን” ሲሉ በመግለጫቸው አንስተዋል።

ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በሀገራዊ ምክክሩ በንቃት እንዲሳተፉ ጥሪ ቀረበ።
Next articleባለስልጣኑ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለመውጫ ፈተና አስፈላጊውን ዝግጅት እንዲያጠናቅቁ አሳሰበ።