
ባሕር ዳር: ሰኔ 20/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በሀገራዊ ምክክሩ ላይ በንቃት እንዲሳተፉ ጥሪ አቀረበ፡፡
ኮሚሽኑ ጉዳዩን አስመልክቶ ባስተላለፈው መልዕክት በኢትዮጵያ በተለያዩ የፖለቲካ እና የሃሳብ መሪዎች እንዲሁም የኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል እጅግ መሠረታዊ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የሃሳብ ልዩነት እና አለመግባባት እንዳለ ይታያል ብሏል፡፡
ይህንን ልዩነት እና አለመግባባት መፍታትና ሀገራዊ መግባባት ላይ መድረስ አስፈላጊ መሆኑንም አጽንኦት ሰጥቷል፡፡
እጅግ መሠረታዊ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ አካታች ሀገራዊ ምክክሮችን በማካሄድ የተሻለ ሀገራዊ መግባባትን ለማምጣት፣በሂደትም የመተማመንን እና ተቀራርቦ የመሥራት ባሕልን ለማጎልበት እንዲቻል ገለልተኛ የሆነ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ተቋቁሞ ሥራ መጀመሩ ተመላክቷል፡፡
ስለሆነም በውጭ ሀገራት የሚትኖሩ ኢትጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በሙሉ ይህንን ታሪካዊ አጋጣሚ ተጠቅመው በኢትዮጵያ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ላይ ወሳኝ ሚና ይኖረዋል ተብሎ በሚጠበቀው ሀገራዊ ምክክር ላይ በንቃት እንዲሳተፉ ኮሚሽኑ ጥሪ አቅርቧል፡፡
ይህንንም ለማስፈፀምም ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የበይነ መረብ (ዙም) ስብሰባ ለማድረግ ማቀዱን ነው ያስታወቀው፡፡
በዚህ መሰረትም በአፍሪካ፣ በመካከለኛው ምሥራቅና አውሮፓ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጋር ሐምሌ 1 ቀን፣ 2015 (ሐምሌ 8 ቀን 2023)፣ በሰሜን እና ደቡብ አሜሪካ እንዲሁም በኦሺንያ እና እስያ ከሚኖሩ ጋር ደግሞ በሐምሌ 2 ቀን፣ 2015 (ሐምሌ 9 ቀን 2023) የበይነ መረብ (ዙም) ስብሰባ እንደሚካሄድ ተገልጿል፡፡
በስብሰባው ላይ ለመሳተፍ ምዝገባው ከሰኔ 20 እስከ 29 ቀን 2015 ዓ.ም (ሰኔ 27-ሐምሌ 6 ቀን 2023) የሚካሄድ መሆኑን የኮሚሽኑ መረጃ ያመላክታል፡፡
ከስብሰባው አንድ ቀን በፊት የስብሰባው ሊንክ ተመዝጋቢዎች በመመዝገቢያው ቅፅ ላይ ባሰፈሩት የኢሜል አድራሻ እንደሚላክ ተጠቁሟል፡፡
የስብሰባዎቹ ሰዓት ለአፍሪካ፣ መካከለኛው ምሥራቅና አውሮፓ በኢትዮጵያ አቆጣጠር ከቀኑ 9 ሰዓት፤ ለኦሺንያ እና እስያ ከጠዋቱ 4 ሰዓት እና ለሰሜን እና ደቡብ አሜሪካ አመሻሽ ላይ በ12 ሰዓት እንደሚሆን ተጠቅሷል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!