ትምህርት ሚኒስቴር በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸውን 45 ትምህርት ቤቶች በክልሉ እያስገነባ መኾኑ ተገለጸ፡፡

37

ባሕር ዳር: ሰኔ 20/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ባለፉት ሦስት ዓመታት በሰሜን ኢትዮጵያ አካባቢዎች በተከሰተው ጦርነት እና ግጭት ምክንያት በአማራ ክልል ከተጎዱ አገልግሎት ሰጭ ተቋማት መካከል ትምህርት አንዱ ነው፡፡ ቀድሞውንም በርካታ የትምህርት ተቋማት ከደረጃ በታች የኾኑበት ክልሉ በጦርነቱ የደረሰበት ውድመት እና ጉዳት ችግሩን አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንዲደርስ አድርጎታል፡፡

ከጦርነቱ ማግስት ጀምሮ የተደረጉ የዳሰሳ ጥናቶች እንደሚያመላክቱት በጦርነቱ ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸው የትምህርት ተቋማት የተለያየ ደረጃ አላቸው፡፡ በርካታ ትምህርት ቤቶች ሙሉ በሙሉ ጉዳት ሲደርስባቸው በርካቶቹ ደግሞ ከፊል ጉዳት አጋጥሟቸዋል፡፡ በንብረት ደረጃ ግን ሁሉም ወረራ በተካሄደባቸው አካባቢዎች ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ ያላቸው የትምህርት ቁሳቁስ ከጥቅም ውጭ ኾኖባቸዋል ያሉን የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ሕዝብ ግንኙነት እና ጽሕፈት ቤት ኅላፊ አቶ ጌታቸው ቢያዝን ናቸው፡፡

ወረራ በተካሄደባቸው አካባቢዎች 4 ሺህ 86 ትምህርት ቤቶች ሙሉ በሙሉ እና በከፊል ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ ጉዳት ከደረሰባቸው ትምህርት ቤቶች መካከል 1 ሺህ 200 ትምህር ቤቶች ሙሉ በሙሉ ወድመዋል ያሉት የሕዝብ ግንኙነት ኅላፊው 2 ሺህ 886 ትምህርት ቤቶች ደግሞ በከፊል ጉዳት የደረሰባቸው ናቸው፡፡ ሙሉ በሙሉ ውድመት የደረሰባቸውን ትምህርት ቤቶች ግንባታ እና ከፊል ጉዳት የደረሰባቸውን ደግሞ ጥገና ለማካሄድ እየተሰራ መኾኑን አቶ ጌታቸው በተለይም ለአሚኮ ገልጸዋል፡፡ የአማራ ክልል በጦርነት ጉዳት የደረሰባቸው አካባቢዎች መልሶ ማቋቋምና ልማት ፈንድ ጽሕፈት ቤት 332 ሚሊዮን ብር በሚደርስ ወጭ 22 ትምህርት ቤቶችን እያስገነባ ነው ተብሏል፡፡

በሌላ በኩል የተለያዩ የሲቪክ ማኀበራት 26 ትምህርት ቤቶችን በአዲስ እያሰገነቡ መኾኑን የገለጹት የሕዝብ ግንኙነት ኅላፊው ትምህርት ሚኒስቴር በጦርነቱ ሙሉ በሙሉ የወደሙ 1 ሺህ 200 ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት ቃል ገብቷል ነው ያሉት፡፡ በተያዘው ዓመትም 45 ትምህርት ቤቶችን እያስገነባ ነው ተብሏል፡፡ ትምህርት ሚኒስቴር የተለያዩ የድጋፍ ፈንዶችን እና አጋር አካላትን በማስተባበር ቃል የገባቸውን ትምህርት ቤቶች ለመገንባት እንደሚሰራ ተሰፋ አለን ያሉት የሕዝብ ግንኙነት ኅላፊው ትምህርት ቤቶቹ በሚገነቡባቸው አካባቢዎች ያለው ሕዝብ ትብብር፣ አብሮ መስራት እና ኅላፊነትን መወጣት እንደሚጠበቅበት አቶ ጌታቸው ገልጸዋል፡፡

በጦርነቱ ጉዳት በደረሰባቸው አካባቢዎች ከፊል ጉዳት የደረሰባቸውን ትምህርት ቤቶች ለመጠገን እየተሰራ ነውም ተብሏል፡፡ የ126 ትምህርት ቤቶች ጥገና እየተካሄደ ነው ያሉት አቶ ጌታቸው ከደረሰው ጉዳት እና ውድመት አንጻር እስካሁን ያለው ሂደት በቂ ነው ባይባልም ጅምሮችን አጠናክሮ ማስቀጠል ይጠይቃል ነው ያሉት፡፡

በክልሉ ትምህርት ቤቶችን ገንብቶ በማስረከብ እንደ አልማ ያሉ የካበተ ልምድ ያላቸው ተቋማት አሉ፡፡ ኅላፊነታቸውን እየተወጡ ያሉ ተቋማትን እና ባለሃብቶችን ተሞክሮ በመውሰድ ትምህር ቤቶች ግንባታ እና ጥገና ላይ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ አቶ ጌታቸው ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleየፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ.ር )ከፈረንሳይ ንግድ ምክር ቤት አባላት ጋር ተወያዩ።
Next articleበውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በሀገራዊ ምክክሩ በንቃት እንዲሳተፉ ጥሪ ቀረበ።