“ኡድሂያ-የአሏህ የበረከት መንገድ”

154

ባሕር ዳር: ሰኔ 19/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በእስልምና ሃይማኖት ትልቅ ቦታ ካላቸው ሃይማኖታዊ በዓላት መካከል የዒድ አል አድሃ (ዓረፋ) በዓል አንዱ ነው።

ኡድሂያ በዓረፋ በዓል ልዩ ነው፣ የቃል ኪዳን ማሰሪያ፣ የፍጹም አማኝነት መገለጫ ፣ የፈጣሪን ትዕዛዝ የመፈጸም ጥግ ማሳያ ነውና በአሏህ ዘንድ ትልቅ ዋጋን ያስገኛል ይሉታል የሃይማኖቱ አስተማሪዎች።

ኡድሂያ ምንድን ነው እንዴትና ለምን ይፈጸማል ኡስታዝ ኡስማን ጌጡ የሰጡንን ማብራሪያ ይዘናል።

ኡስታዝ ኡስማን እንደሚሉት የዓረፋ በዓል መነሻ የአደምና ሃዋ ከጀነት ወደ ምድራዊ ዓለም መውረድና ዳግም መገናኘት ጋር የተያያዘ ነው።

የበዓሉ መጠሪያ ለመኾን የበቃው ተራራ አደምና ሐዋ ከጀነት ከወረዱ ከዓመታት በኋላ ዳግም የተገናኙበት የዓረፋ ተራራ ነው ይባላል።

ከበዓሉ ትልልቅ ታሪካዊ ክዋኔዎች መካከል አንዱ ኡዱሁያ-የእርድ ሥነ-ሥርዓት መኾኑን ኡስታዝ ኡስማን ጌጡ ይናገራሉ።

ኡስታዝ ኡስማን የሃይማኖቱን አስተምህሮ እያጣቀሱ እንደሚያብራሩት የዓረፋ በዓል ኡዱሁያ የእርድ ሥነ-ሥርዓት መነሻው የነብዩ ኢብራሂምና የልጁ እስማኤል ታሪክ ነው።

ነብዩ ኢብራሂም ከፈጣሪ በተገለጠላቸው ትዕዛዝ መሠረት ልጃቸውን እስማኤልን እንዲሰው የተደረገበት ከአሏህ መልእክት ጋር የተያያዘ ነው ይላሉ ኡስታዝ ኡስማን።

በአሏህ ትዕዛዝ ልጃቸውን ለማረድ የወሰኑት ነብዩ ኢብራሂም ታማኝነትን ፈጽመው የፈጣሪን ትዕዛዝ ፈጻሚ ጻድቅ ሰው መኾናቸው በፈጣሪ ዘንድ ርህራሔን አወረደ ነው የሚሉት ኡስታዝ ኡስማን።

እኒያ ታማኝና ታዛዥ ነቢይ ኢብራሂም ይላሉ ኡስታዝ ኡስማን የአሏህን ትዕዛዝ ለመፈጸም ቀናኢ ሰው ስለኾኑ ልጃቸው እስማኤል መሰዋዕት መኾናቸው ቀርቶ ከጀነት ለሚያርዱት በግ እንደወረደላቸው ቁራዓን ያስረዳል ብለዋል።

ይህን ታሪክ መነሻ በማድረግ ሕዝበ ሙስሊሙ በዓረፋ በዓል ኡዱሁያ የእርድ ሥነ-ሥርዓት ይፈጸማል ነው የሚሉት ኡስታዙ።

ኡስታዝ ኡስማን እንደሚሉት በዓረፋ በዓል አድሂያ መፈጸም እንደሚገባ ነብዩ አዝዘዋል።

“በበዓሉ እረዱ ነፍሳችሁንም ንጹህ አድርጉ አሳምሩ ብለዋል ነብዩ ሙሐመድ (ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም)”ነው ያሉት ኡስታዝ ኡስማን።

እያንዳንዱ ሙስሊም ሲያርድ የምድር ላይ ቆይታው በጽድቅ ሚዛን ዋጋ የሚያስገኝ እንደኾነም ነው የሚያስረዱት።

የሚችል አማኝ ሁሉ ኡድሂያ መፈጸም እንደሚገባው ሃይማኖቱ ያዝዛል የሚሉት ኡስታዝ ኡስማን በአቅም ማጣት ሳያርድ የቀረ ግን ሃጢያት ይኾንበታል ማለት እንዳልኾነም አስረድተዋል።

በዓረፋ ሐጂ ላይ ያለም መካ ላይ ኾኖም ቢኾን ኡድሂያ ቢያደርግ ከአሏህ ድርብ በረከትን ያገኛል ነው የሚሉት።

ነብዩ እርድን አስመልክቶ እንደተናገሩት ይላሉ ኡስታዝ ኡስማን “ሶላት ከተደረገ በኋላ ነው እርድ – ኡዱሁያ የሚፈጸመው።

ኡድሂያ -የአሏህ የበረከት መንገድ ስለመኾኑም ነው ኡስታዝ ኡስማን የሚያስረዱት።

ነብዩ እንደተናገሩት ይላሉ ኡስታዝ ኡስማን “ሶላት የሰገደ፣ እርዱንም ያረደ የእኛን መንገድ የያዘ ነው ብለዋል፤ ከሶላት በፊት ያረደ ግን እንደ አዘቦቱ ጊዜ እንደታረደ የሚቆጠር ነው” ብለዋል ።

የኡድሂያ እርድ ማለት የኢደል አል አድሀ ዓረፋ ቀን እና በቀጣዮቹ ሦስት ተከታታይ ቀናት ውስጥ ወደ አላህ ለመቃረብ የሚካሄድ የእርድ ኢባዳ (የአምልኮ) ክንውን ነው ይሉታል።

የኡድሂያውን ሥጋ ለቤት፣ ለስጦታ እና ለሰደቃ አድርጎ ሦስት ቦታ መከፋፈሉ ሱና እንደኾነም ይገለጻል።

ይህ ማለት ግን እንደ አስፈላጊነቱ ለሦስቱም ያውለዋል ማለት እንጂ ሦስት እኩል ቦታዎች ይከፋፍለዋል ማለት እንዳልኾነም ነው የሚያስረዱት።

ኡስታዝ ኡስማን እንዳሳሰቡት ማንኛውም ሙስሊም በዓሉን ሲያከብር ማረድ ያልቻሉትን፣ አቅመ ደካሞችን በማሰብ፤ ሃይማኖታዊ ትዛዙን መፈጸም ይገባል።

በተባረከው ቀን ሶላትን በመስገድ፣ ታላላቆችን በማክበር፣ ለሰው ልጆች ሁሉ ክብር በመስጠት በዓሉን ማክበር ይገባል ነው ያሉት።

ኡስታዝ ኡስማን በዓረፋ በዓል የታመሙትን፣ የተቸገሩትንና አቅመ ደካሞችን በበዓሉ ተከፍተውና ተክዘው እንዳይውሉ በመርዳት የደስታቸው ምንጭ መኾን ይገባል ሲሉም አሳስበዋል።

ዘጋቢ:-ጋሻው አደመ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleብሩህ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ውድድር የሽልማት ሥነ ሥርዓት በመካሄድ ላይ ይገኛል።
Next articleየፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ.ር )ከፈረንሳይ ንግድ ምክር ቤት አባላት ጋር ተወያዩ።