
ባሕር ዳር: ሰኔ 19/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ማሰልጠን፣ መሸለም ፣ ማብቃት በሚል መርኅ የሚከናወነውና በሁሉም ክልሎች ከወረዳ ጀምሮ ሲካሄድ የቆየው ብሩህ ሀገር አቀፍ የንግድ ሥራ ፈጠራ ሃሳብ ውድድር አንድ ሺህ 137 የክልል እና የዩኒቨርሲቲ አመልካቾችን በማሳተፍ የሥራ ፈጠራ ሃሳባቸውን ሲያወዳድር ቆይቶ 50ዎቹን ለሽልማት አብቅቷል።
እየተካሄደ በሚገኘው አራተኛው ብሩህ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ውድድር የሽልማት መርሐ ግብር ላይ ስለ ውድድሩ አካሄድ ማብራሪያ የሰጡት በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ዴኤታ አቶ ንጉሡ ጥላሁን ናቸው።
በንግግራቸውም ማሰልጠን፣ መሸለም ፣ ማብቃት በሚል መርኅ የሚከናወነው ውድድር በ2013 ዓ.ም ተጀምሮ ሰባት ውድድሮች መከናወናቸውን አስታውሰዋል።
ከዚህ ቀደም በተካሄዱ 7 ሀገር አቀፍ እና ክልላዊ ውድድሮች በአጠቃላይ 2,412 አመልካቾች የተሳተፉ ሲሆን ለ400 ሃሳብ ባለቤቶች ወይም 552 ወጣቶች የቡትካምፕ ስልጠና ተሰጥቷል።
በአጠቃላይ ለ 167 ምርጥ ሃሳቦች የ አንድ ሚሊዮን 518 ሺህ ዶላር የገንዘብ ሽልማት ተበርክቷል ብለዋል።
ብሩህ የሥራ ዕድል ፈጠራ ኃሳቦች ውድድር ፕሮግራም በኢትዮጵያ በሥራ ዕድል ፈጠራ ዘርፍ እና በማኅበረሰቡ ውስጥ የሚታዩ ቁልፍ ችግሮችን ለመፍታትና የሥራ ዕድሎችን ለመፍጠር የሚችሉ አዳዲስ ሀሳቦች ይዘው የሚመጡ ወጣቶችን ለማበረታታት የተዘጋጀ የውድድር መርሐ ግብር መሆኑንም ገለጸዋል።
እስካሁን በነበሩት ውድድሮች ለአሸናፊዎች የንግድ ማብቃት ተግባር መከናወኑን የተናገሩት አቶ ንጉሡ ለዚህ ዓመት ብሔራዊ ውድድር 50 ተሸላሚዎች ለቀጣዮቹ 3 ወራት የንግድ ሥራ ልማት ድጋፍ ይደረግላቸዋል ብለዋል።
ብሩህ ኢትዮጵያ ሀገር አቀፍ የንግድ ሥራ ፈጠራ ሃሳብ ውድድር 1,137 የክልል እና የዩኒቨርሲቲ አመልካቾችን በማሳተፍ የሥራ ፈጠራ ሃሳባቸውን ሲያወዳድር መቆየቱን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያሳያል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!