ከ1 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ ምዕመናን ለሐጂ ሳዑዲ አረቢያ ገብተዋል፡፡

51

ባሕር ዳር: ሰኔ 19/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በመጭው ረቡዕ ለሚፈጸመው የሐጂ ሥርዓት ከ1 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ ምዕመናን ሳዑዲ አረቢያ ገብተዋል፡፡ በዘንድሮው የሐጂ ሥርዓት ሳዑዲ አረቢያ ከ2 ሚሊዮን በላይ ምዕመናንን ለመቀበል መዘጋጀቷ ተሰምቷል፡፡

የሀገሪቱ የፓስፖርት ጉዳዮች ጀኔራል ዳይሬክተር ዛሬ በሰጠው መግለጫ 1 ሚሊዮን 626 ሺህ 500 ምዕመናን ለሐጂ ሥርዓት ሳዑዲ አረቢያ ገብተዋል ብሏል፡፡ ሙስሊም ተጓዦቹ ከዓለም ኹሉም አካባቢ በአየር፣ በባሕር እና በየብስ ተጓጉዘው ወደ ግዛቲቱ መድረሳቸውን ገልጸዋል፡፡

እስከ ዛሬ ወደ ሳዑዲ አረቢያ ከደረሱት የሐጂ ሥርዓት ታዳሚዎች መካከል 1 ሚሊዮን 559 ሺህ 053 የውጭ ሀገራት ዜጎች ናቸው ተብሏል፡፡ በነዳጅ ሃብት የበለጸገችው ሳዑዲ አረቢያ በዘንድሮው የሐጂ ጉዞ ከ2 ሚሊዮን በላይ የሐጅ ተጓዦችን ለመቀበል እንደተዘጋጀችም አናዶሉ የዜና ወኪል ዘግቧል፡፡

ሳዑዲ አረቢያ ላለፉት ሦስት ዓመታት የዓለም ሀገራት የጤና ስጋት በሆነው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የሐጂ ሥርዓትን በከፊል ክልከላ አድርጋ ቆይታለች፡፡ ባለፈው ዓመት ሳዑዲ ለሐጂ ሥርዓት 900 ሺህ ምዕመናንን ተቀብላ ነበር ተብሏል፡፡ እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር 2020 10 ሺህ በ2021 ደግሞ 60 ሺህ የሐጂ ተጓዦችን ብቻ ተቀብላለች፡፡

ወደ መካ ካዕባ የሚደረገው የሐጂ ጉዞ ከእስልምና ሃይማኖት አምስት ምሰሶዎች ውስጥ አንዱ ነው፡፡ አንድ ሙስሊም በሕይዎት ዘመኑ ከቻለ እና አቅሙ ከፈቀደ ቢያንስ አንድ ጊዜ ሐጂ ያደርጋል።

በታዘብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየወጣቶች የሰላም ፌስቲቫል በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው፡፡
Next article“በፈረንጆቹ 2030 የንጹህ መጠጥ ውኃ አቅርቦትን ለሁሉም ለማዳረስ እየተሠራ ነው” የውኃ እና ኢነርጅ ሚኒስቴር