የወጣቶች የሰላም ፌስቲቫል በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው፡፡

73

አዲስ አበባ: ሰኔ 19/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የኢፌዴሪ ሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ስካውት ማኅበርና ከአክሽን ኤይድ ኢትዮጵያ ጋር በጋራ በመኾን ለኢትዮጵያ ሰላም ግንባታ የወጣቶች ሚናን ማሳደግ በሚል መሪ ሀሳብ የወጣቶች የሰላም ፌስቲቫልን እያካሄደ ነው፡፡

በፌስቲቫሉ ከተለያዩ ከተሞች የመጡ ወጣቶችና የሚኒሊክ ትምህርት ቤት ማርሽ ባንድ ተሳታፊ ኾነዋል፡፡ ፌሲቲቫሉ በሰላም እጦት የተጎዱ ማኅበረሰቦችን ለመርዳትና ወደ ነበሩበት የሰላም አየር ለመመለስ ሚናው ከፍተኛ መኾኑ ተገልጿል፡፡

በፌስቲቫሉ ላይ የተገኙት የኢፌዴሪ ሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋየ (ዶ.ር) በሰው ሠራሽና በተፈጥሮ ምክንያቶች የተፈጠሩ አለመግባባቶች ለሕፃናትና ለእናቶች ስብራት መንስኤ ኾነዋል ብለዋል፡፡ ሚኒስትሯ በነበረው የሰላም እጦት የተጎዱ ማኅበረሰቦችን ለመርዳትና ወደ ነበሩበት የሰላም አየር ለመመለስ ከወጣቶች ትልቅ ኀላፊነት ይጠበቃል ነው ያሉት፡፡

የነገዋን ኢትዮጵያን ለመገንባት ለዕድገት እና ለሰላም አንቅፋት የኾኑ አለመግባባቶችንና ልዩነቶችን በውይይት ለመፍታት ወጣቶች ምክክርን እና ውይይትን ባሕል ሊያደርጉ እንደሚገባም ዶክተር ኤርጎጌ አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ስካውት ማኅበር ወጣቶች ለሰላም ዘብ እንዲቆሙ እያደረገ ስላለው እንቅስቃሴ አመሥግነዋል፡፡ እንደ ስካውት ያሉ ማኅበራት ወጣቱን ለሰላም ዘብ ለማቆም ከዚህ በበለጠ ሊጠናከሩ እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡

ፌስቲቫሉ ለሁለት ቀናት እንደሚቆይ ተጠቅሷል፡፡

ዘጋቢ፡- ራሔል ደምሰው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየ2015 ዓመት የአማራ ክልል እግር ኳስ ክለቦች ሻምፒዮና በወልድያ ከተማ እየተካሄደ ነው።
Next articleከ1 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ ምዕመናን ለሐጂ ሳዑዲ አረቢያ ገብተዋል፡፡