በክረምት በጎ ፈቃድ 108 ሺህ ዩኒት ደም ለመሰብሰብ ታቅዷል።

57

👉አንድ ሰው 450 ሚሊ ሊትር ደም ሲለግስ የሦስት ሰው ሕይወት ማዳን ይችላል

ባሕር ዳር: ሰኔ 19/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ከአንድ ሳምንት በኋላ ተግባራዊ ማድረግ በሚጀመረው የክረምት በጎ ፈቃድ የደም ልገሳ መርሐግብር 108 ሺህ ዩኒት ደም ለመሰብሰብ መታቀዱን የኢትዮጵያ ደምና ኅብረህዋስ ባንክ አገልግሎት አስታውቋል።

በበጀት ዓመቱ 11 ወራት 320 ሺህ ዩኒት ደም መሰብሰቡ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ የደምና ኅብረህዋስ ባንክ አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሀብታሙ ታዬ እንደገለጹት፤ በክረምት ወራት ትምህርት ቤቶች ዝግ በመኾናቸውና ወቅቱ ቅዝቃዜ ከመኾኑ ጋር ተያይዞ የደም እጥረት እንዳያጋጥም እየተሠራ ነው።
ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ እስከ መስከረም 30 ቀን 2016 ዓ.ም በሀገር አቀፍ ደረጃ 108 ሺህ ኒት ደም ለመሰብሰብ መታቀዱን አስታውቀዋል።

ክረምት ሲገባ የደም ለጋሾች ቁጥር እንደሚቀነስ የበፊት ተሞክሮዎች ያሳያሉ ያሉት አቶ ሀብታሙ፤ በአደባባዮች፣ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ባልኾኑ ተቋማት ደም የማሰባሰብ ሥራ በትኩረት ይሠራል ብለዋል።

እንደ አቶ ሀብታሙ ገለጻ፣ በአዲስ አበባ ከተማ ሁሉም ክፍለ ከተሞች ከተደራጀው ብሔራዊ የደም ለጋሾች ማኅበርና ወጣቶች ጋር በጋራ በመኾን በዘንድሮው ክረምት በጎ ፈቃድ ደም ለጋሾችን በማስተባበር በሚቀጥለው ሳምንት የማሰባሰብ ሥራ እንደሚጀመር አስታውቀዋል።

በዚህም በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ 37 ሺህ ዩኒት ደም ለመሰብሰብ የታቀደ ሲሆን፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ ደግሞ 108 ሺህ ዩኒት ደም ለመሰብሰብ ታቅዷል ብለዋል።

በበጀት ዓመቱ 11 ወራት 419 ሺህ ዩኒት ደም ለመሰብሰብ ታቅዶ 320 ሺህ ዩኒት ደም የተሰበሰበ ሲሆን፤ የእቅዱን 76 በመቶ ብቻ ማሳካት መቻሉን ገልጸዋል።

የበጀት ዕጥረት፣ የደም ለጋሾች ተሳትፎ በተወሰኑ ወራት ዝቅተኛ መኾን እና የአንዳንድ ክልሎች አፈጻጸም ዝቅተኛ መሆን ከዕቅድ በታች አፈጻጸም እንዲመዘገብ ምክንያት ሆኗል ብለዋል።

በክልል ደረጃ ያለውን የደም ልገሳ አፈጻጸም በተመለከተ የተወሰኑ ክልሎች ላይ በበጀት እጥረት ምክንያት ደካማ እንቅስቃሴ መኖሩን የተናገሩት አቶ ሀብታሙ፤ በአዲስ አበባ፣ በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች የተሻለ አፈጻጸም እንዳለ ተናግረዋል። በአንጻሩ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ አፋር፣ ጋምቤላ፣ ሲዳማ እንዲሁም ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ላይ ደግሞ የደም ልገሳ አፈጻጸሙ ዝቅተኛ ነው ብለዋል።

አንድ ሰው 450 ሚሊ ሊትር ደም ሲለግስ የሦስት ሰው ሕይወት ማዳን እንደሚችል ማኅበረሰቡ ተረድቶ የደም ልገሳ በጎ ተግባር ላይ በንቃት እንዲሳተፍም አቶ ሀብታሙ ጥሪ ማቅረባቸውን ኢፕድ ዘግቧል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የትምህርት ቤቶችን መሰረተ ልማት ለማሻሻል ሀገር አቀፍ ሕዝባዊ ንቅናቄ ሊካሄድ ነው” ትምህርት ሚኒስቴር
Next articleየቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ ቡና ጨዋታ በአቻ ውጤት ተጠናቀቀ