
ባሕር ዳር: ሰኔ 19/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የትምህርት ቤቶችን መሰረተ ልማት ለማሻሻል የትምህርት ባለድርሻዎችንና ኅብረተሰቡን ያሳተፈ ሀገር አቀፍ የህዝብ ንቅናቄ ሊያካሄድ መሆኑን የትምህርት ሚኒስቴር አስታውቋል።
ሀገር አቀፍ ንቅናቄው ሰኔ 25 ቀን 2015 ዓ.ም የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በይፋ እንደሚጀመር ተገልጿል።
የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ ሀገር አቀፍ ንቅናቄው ኅብረተሰቡ የትምህርት መሠረተ-ልማትን በማሻሻል የመማር ማስተማሩን ሂደት በባለቤትነት እንዲደግፍ ለማድረግ መኾኑን ገልፀዋል።
የትምህርት ቤቶችን መሰረተ ልማት የማሻሻል ሥራ ለመንግሥት ብቻ የተተወ ኃላፊነት አለመኾኑን የጠቆሙት ሚኒስትሩ በየደረጃው ያለው ማኅበረሰብና ልዩ ልዩ አካላት ተሳትፏቸውን ሊያሳድጉ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
አብዛኞቹ የመጀመሪያ፣ መካከለኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ንጹህና በቂ ውኃ እንደማያገኙ፣ የኤሌክትሪክ ፣ የመፀዳጃ ፣ የመማሪያ ፣ የቤተ መጻሕፍት ፣ የቤተ ሙከራ ፣ የስፖርት ማዘውተሪያና ሌሎችም ችግሮች እንዳሉባቸው ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
በሀገሪቱ የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሚስተዋሉ ዋነኛ የትምህርት መሰረተ ልማት ችግሮችን ለመፍታት እየተሠራ መሆኑንም አስታውቀዋል።
በዚህም ባለሀብቶች ፣ ታዋቂ ግለሰቦች ፣ አርቲስቶች፣ የዲያስፖራ አባላት፣ ልዩ ልዩ አደረጃጀቶች፣ መንግሥታዊና መንግስታዊ ያሆኑ የበጎ አድርጎት ድርጅቶች ፣ ማህበራትና ሌሎችም የትምህርት ሥራ አጋሮችና ባለድርሻዎች በንቅናቄው የድርሻቸውን እንዲወጡ ፕሮፌሰር ብርሀኑ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የሀገር አቀፍ ንቅናቄው ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ሰኔ 25 ቀን 2015ዓ.ም እንደሚካሄድ ሚኒስቴሩ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ አስታውቋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!