
ባሕር ዳር: ሰኔ 19/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ከመላው የዓለም ማዕዘናት የሚነሱ በርካታ የእስልምና እምነት ተከታዮች የሐጅ እና ዑምራ ሃይማኖታዊ ሥርዓት ለመከወን በሳዑዲ አረቢያ ምዕራባዊ ክፍል ወደሚገኘው እስላማዊ ቅዱስ ከተማ – መካ ይጓዛሉ። በመካ ከተማ ሐረም መስጊድ ውስጥ በነብዩ ኢብራሒም የተገነባ “ካዕባ” የተባለ ጥንታዊ የአሏህ ቤት አለ።
የእምነቱ ተከታዮች ከሚኖሩበት ዓለም በመነሳት ሩቅ ሸለቆ አቋርጠው ወደ መካ የሚጎርፉት በካዕባ ያለውን የአሏህ ሰላም እና እዝነት በጥንታዊው ቤት ውስጥ ለማግኘት ነው።
በእስልምና ሃይማኖት ምዕመኑ ይፈጽማቸው ዘንድ ግዴታዎች የኾኑ አምስት መሰረታዊ ጉዳዮች አሉ። እነሱም የአሏህን አምላክነት አምኖ መቀበል፣ መጾም፣ሶላት መስገድ፣ ከገንዘብ ላይ ዘካ ማውጣት እና ወደ አሏህ ቤት መሐጀጅ ናቸው።
የአማራ ክልል እስልምና ጉዳይ ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት ሼህ ሙሐመድ አንዋር እንደነገሩን ሐጂ ማለት አቅሙ የፈቀደለት አማኝ ኹሉ በመካ ተገኝቶ በጥንታዊው የአሏህ ቤት ካዕባ ውስጥ የሚያመልክበት ሥርዓት ነው።
ሐጂን በሕይወት አንድ ጊዜ መፈጸም ችሎታ ባለው ሁሉ ግዴታ ነው። ሐጂ ሀብታሙ፣ ድሃው፣ ትልቁ፣ ትንሹ፣ ባለስልጣኑ እና ሌላውም ኹሉም ሁለት ነጭ ነጠላ ልብሶችን ማለትም ሽርጥ እና ኢህራም ብቻ አድርጎ ረጅሙን ጉዞ የሚያስታውስበት የአምልኮ ሥርዓት ስለመኾኑ ሼህ ሙሐመድ አንስተዋል። “ሐጅ የሰው ልጆች ሁሉ እኩል ስለመኾናቸው የሚመሰከርበትም ነው” ሲሉም ገልጸውታል።
ወደ መካ የተጓዙ ሐጃጆች ኹሉ ከተከበረው መስጊድ ሲደርሱ ለመግባት ቀኝ እግራቸውን ያስቀድማሉ። ” የአሏህ እዝነትና ሰላም በመልዕክተኛው ላይ ይውረድ፤ ጌታየ ኾይ ለወንጀሌ ምህረትህን ለግስልኝ፤ የእዝነትህን በር ክፈትልኝ…” እየተባለ በስህተት ወይም በድፍረት ስለተሠራ ኃጢአት መሰረዝ አምላክ ይለመንበታል።
እንደ ሼህ ሙሐመድ ገለጻ የሐጅ ቱሩፋቶች በርካታ ናቸው። ሐጅ ያለፉ በደሎችን ይሰርዛል።ሐጅ እና ዑምራውን አሏህ በሚፈልገው መልኩ ያደረገ ሰው እናቱ እንደወለደችው ዕለት ከኃጢአት ፀድቶ ይመለሳል። ሥርዓቱን ጠብቆ የተካሄደ ሐጅ ተቀባይነት ያገኛል። ከአንድ ዑምራ እስከ ቀጣዩ ዑምራ በመካከላቸው የሚፈጸመውን ኃጢአትም ያስፍቃል። “ተቀባይነት ያገኘ ሐጅ ዋጋው ጀነት ብቻ ነው” ይላሉ ሼህ ሙሐመድ ።
ሼህ ሙሐመድ ሐጅ ለማድረግ ሕጻን፣ አዋቂ፣ ሴት፣ ወንድ፣ ሃብታም ወይም ድሃ መኾን አያግድም ብለዋል። ለማንኛውም ሙስሊም የተፈቀደ ነው። ለሁሉም የእምነቱ ተከታዮችም ግዴታ አይደለም። ከሚኖርበት ቦታ እስከ መካ ደርሶ ለመመለስ ስንቅ ማዘጋጀት እና የሚጓዝበትን ወጭ መሸፈን በቻለ የእምነቱ ተከታይ ላይ ግን ሐጅ ሃይማኖታዊ ግዴታ ነው ብለዋል ሼህ ሙሐመድ።
ለመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች እንኳን ለዒድ አል አድሃ (አረፋ) በዓል አደረሳችሁ!
ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
