
ባሕር ዳር: ሰኔ 19/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር) ማሕበራዊ ሚዲያውን በአግባቡና በሰለጠነ መንገድ መጠቀም ካልተቻለ እጅግ የከፋ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ እንደሚያስከትል በማሕበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልእክት አሳስበዋል፡፡
የርእሰ መስተዳድሩ ሙሉ መልእክት ቀጥሎ ቀርቧል፦
ማሕበራዊ ሚዲያን ለበጎ ዓላማ እንጠቀምበት!
ከቴክኖሎጂ እድገትና መዘመን ጋር ተያይዞ ዘርፍን የሚጠቀሙ ዜጎች ቁጥር ከጊዜ ወደጊዜ ጨምሯል። የኢንተርኔት አገልግሎት ተደራሽነትን ተከትሎ ማሕበራዊ ሚዲያው ተጽዕኖ ፈጣሪና ቀዳሚ የሕዝብ የመገናኛ አማራጭ ሆኗል። ይህም በመሆኑ ተፈላጊ መረጃዎችን በፍጥነት በማድረስ በሕዝብ ሕልውና ውስጥ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከፍ ያለ ነው።
የሰዎችን ግንኙት ቀላልና ቀልጣፋ አድርጓል። ጊዜ፣ ጉልበትና ሃብታቸውን ሳያባክኑ በየአሉበት ሁነው በፍጥነት እንዲገናኙ አድርጓል። ይህ እድገት አንዱ የስልጣኔ መገለጫ ነው። ለኢኮኖሚያችን እድገትም ትልቅ አቅም ነው። ይህንን መልካም እድል ለሰላም፣ ለልማትና ለሀገር ግንባታ መጠቀም ያስፈልጋል።
ይሁን እንጅ ማሕበራዊ ሚዲያው ለሁለንተናዊ እድገት ሚናው የጎላ ቢሆንም በአግባቡና በሰለጠነ መንገድ መጠቀም ካልተቻለ ደግሞ እጅግ የከፋ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ያስከትላል፡፡
በሰለጠነ መንገድ መጠቀም ካልቻልነ ሰላማችን ያናጋል፤ ጥላቻን ያስፋፋል፡፡ የሕዝብን አብሮነት ይሸረሽራል፡፡ መጠራጠርና ልዩነትን በማስፋት ሕዝብን ከሕዝብ በማጋጨት ለሰዎች ሕይወት እልፈት፣ ለሀብትና ንብረት ውድመት ምክንያት ይሆናል፡፡
በተለይም አሁን አሁን ኃላፊነት በጎደለው መንገድ በመጠቀም የተዛቡ፣ በጥላቻና በልዩነት የተሞሉ፣ መሰረት ቢስ ወሬዎችን በማሰራጨት በሕዝብ መካከል ልዩነት በመፍጠር የግጭትና ሁከት መቀስቀሻ መሳሪያ በሆነበት ወቅት ላይ እንገኛለን፡፡
ከልዩነት እና ጥላቻ ደግሞ ጥፋት እንጅ የሚገኝ ትርፍ የለም። ሊኖርም አይችልም። ማህበራዊ ሚዲያውን ለበጎ ዓላማ በማዋል የህዝባችን አብሮነት፣ ወንድማማችነት፣ ተቻችሎና ተከባብሮ የመኖር የቆየ ባህልንና እሴት ይበልጣል ማጠናከሪያና ማቀራረቢያ መሳሪያ ማድረግ ይኖርብናል።
በክልላችንም ዘርፉን ለበጎ ዓላማ በመጠቀም በጋራ የተንቀሳቀሱ ወጣቶችና የበጎ ሃሳብ ባለቤቶች መልካም ስራዎችን ለአካባቢያቸው ሕዝብ አበርክተዋል። በተለያዩ አካባቢዎች ትምህርት ቤትና ጤና ተቋም ሰርተዋል፤ የህዝብ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ገንብተዋል፣ ሰብአዊ ድጋፍ ለሚሹ ዜጎች ድጋፍ አሰባስበው ዜጎችን ከጉስቁልና አውጥተዋል፣ የፈረሱ ተቋማትን ጠግነዋል።
ባሕል፣ ታሪክና እሴቶቻቸውን አስተዋውቀዋል፤ ትልልቅ የፋይናንስ ተቋማትን መስርተዋል። በዚህ መልኩ ሚዲያውን ለበጎ ተግባር በመጠቀም አርአያ ለሆናችሁ ሁሉ ምስጋናችን ላቅ ያለ ነው።
በቀጣይም ይሔንን በጎ ዓላማችሁን አጠናክራችሁ እንድትቀጥሉ እያልኩ፥ የክልላችን ምሁራን፣ ወጣቶች፣ የዘርፍ ተጠቃሚዎችና የሚዲያ ተቋማት ለሀገር ሰላምና እድገት ጉልህ አስተዋጽኦ ያለውን ዘመናዊ ሚዲያ ለበጎ ዓላማ በማዋል የበኩላችሁን ድርሻ እንድትወጡ በራሴና በክልሉ መንግሥት ስም አደራ ለማለት እወዳለሁ።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!