በሕገወጥ የወርቅ ምርት፣ ግብይትና ዝውውር ተሳትፎ የነበራቸው የመንግሥት ሐላፊዎችና የጸጥታ መዋቅር አመራሮች በቁጥጥር ሥር ዋሉ

634

ባሕር ዳር: ሰኔ 18/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በሕገወጥ የወርቅ ምርት፣ ግብይትና ዝውውር ተሳትፎ የነበራቸው 32 የመንግሥት ሐላፊዎችና የጸጥታ መዋቅር አመራሮች፣ አምራቾችና አዘዋዋሪዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት አስታወቀ።

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ በቁጥጥር ስር የዋሉት ግለሰቦች በሕገወጥ መንገድ ወርቅ ሲያመርቱ፤ ሲያዘዋውሩ፣ በጥቁር ገበያ ሲሸጡ እንዲሁም ከውጭ ሀገራት ዜጎች ጋር የጥቅም ትስስር በመፍጠር ብሔራዊ ጥቅምን በሚጎዳ ዕኩይ ተግባር ላይ ተሰማርተው የተገኙት ናቸው።

በቁጥጥር ስር ከዋሉት 32 ግለሰቦች መካከል ስምንቱ የመንግሥትና የጸጥታ መዋቅር አመራሮች፤ ሰባቱ ሕጋዊ ፈቃድን ሽፋን አድርገው በሕገወጥ መንገድ ሲሠሩ የነበሩ አምራቾች እንዲሁም 17 አዘዋዋሪዎችና በሕገወጥ ድርጊቱ የተለያየ ተሳትፎ ያላቸው ሰዎች መሆናቸው አገልግሎት መስሪያ ቤቱ ገልጧል።

ከማዕድን ምርት ጋር በተያያዘ የሚታየውን ሕገወጥነት ለመከላከል የተቋቋመው በሀገር መከላከያ ሚኒስቴር የሚመራው ሀገር ዓቀፍ ካውንስል በሰጠው አቅጣጫ መሰረት የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ከመከላከያ ሠራዊት፣ ከፌዴራል ፖሊስና ከክልል ፖሊስ ኮሚሽኖች ጋር በመሆን ሕገወጦችን የማደን ሥምሪት ወስዶ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን መግለጫው አስታውቋል። ከ15 ቀናት በፊትም በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል በሕገወጥ የወርቅ ምርትና ግብይት ተግባር ተሰማርተው የተገኙ 29 የውጭ ሀገራት ዜጎች በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ማድረጉን በማስታወስ በጋምቤላና በደቡብ ምዕራብ ሕዝቦች ክልልም በተመሳሳይ ሕገወጥ ድርጊት የተሰማሩ ግለሰቦች መያዛቸውን ጠቁሟል።

አገልግሎት መሥሪያ ቤቱ ከእነዚህ ሕገወጦች ጋር ቀጥተኛና ተዘዋዋሪ ግንኙነት የነበራቸውን ግለሰቦች ለመለየት ያልተቋረጠ ክትትልና የመረጃ ማሰባሰብ ሥራዎች ሲያከናውን መቆየቱን መግለጫው አመልክቷል። አገልግሎት መሥሪያ ቤቱ ባደረገው ክትትልና የመረጃ ስምሪትም በሕገወጥ የወርቅ ምርት ግብይትና ዝውውር ተሳትፎ የነበራቸው የመንግሥት ሐላፊዎችና የጸጥታ መዋቅር አመራሮች የተሰጣቸውን ሀገራዊ ተልዕኮ ወደ ጎን በመተው በወርቅ ማምረትና ዝውውር ውስጥ በቀጥታ ተሳትፎ እንደነበራቸው ተረጋግጧል።

የመንግሥት ሥልጣንና ሐላፊነት እንደ ሽፋን በመጠቀም የወርቅ ማምረትንም ሆነ ዝውውሩን አጣምረው በማካሄድ የሀገር ሀብት ሲዘርፉ መቆየታቸው እንደተደረሰበት የጠቆመው መግለጫው፤ በዚህ መንገድ የዘርፉን የተለያዩ የሥራ መስኮች ባልተገባ መንገድ ጠቅልለው በመያዝ ሕጋዊ ስርዓቱንና የፍትሐዊ ተጠቃሚነት መብትን ሲያዛቡ እንደነበርም ገልጿል።

ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የኩምሩክ ወረዳ ገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ፅ/ቤት ኃላፊ ከማል መሀመድ፣ የግብርና ፅ/ቤት ኃላፊ አብዱልከሪም ዬሚዳ፣ የወረዳው ፖሊስ አመራር ምክትል ኮሚሽነር አብዱልሙንየም ሱሌማን እንዲሁም ምክትል አስተዳዳሪ የነበረው አሳይድ አልዕግብ በቁጥጥር ውለዋል። በተመሳሳይ በጋምቤላ ክልልም የዲማ ወረዳ ማዕድን ፅ/ቤት ኃላፊ የሆነው ኡቦንግ ኡቶው ኡጉድ እንዲሁም በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የምዕራብ ኦሞ ዞን የቤሮ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ ከበደ ቡርጂ እና ሌሎችም ከሕገወጥ ድርጊቱ ጋር ትስስር የነበራቸው ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለዋል።

ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ሥር ሲውሉ 21 ክላሽንኮቭ ጠመንጃ ከ420 መሰል ጥይቶች፣ 14 ሽጉጦች ከ62 መሰል ጥይቶች፣ 2 F1 ቦምቦች፣ 250 የብሬን ጥይቶች፣ ወርቅ፣ 8 የወርቅ ሚዛን፣ 5 የወርቅ መፈተሻ ማሽን፣ 2 የወርቅ ማቅለጫ እንዲሁም የተለያዩ የወርቅ ናሙናዎች፣ ኬሚካሎች እንዲሁም በርካታ የተለያዩ ሀገራት ገንዘቦችና የባንክ ደብተሮች በኤግዚብትነት መያዛቸው ታውቋል።

ሕገወጥ የወርቅ ማምረትና ማዘዋወር ተግባሩ ሀገሪቱ ልታገኝ ይገባት የነበረውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ከማሳጣቱ በተጨማሪ የአካባቢው ማኅበረሰብ የበይ ተመልካች እንዲሆን አድርጎታል ያሉት በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የኩሙሩክ ወረዳ ነዋሪዎች፤ መንግሥት የጀመረው ሕግ የማስከበር ተግባር አጠናቅሮ እንቀጥል ጠይቀዋል። ሥራቸውን በሕጋዊ መንገድ እያከናወኑ ያሉ በዘርፉ የተሰማሩ ግለሰቦችም ሕገወጦች ብሔራዊ ባንክ ወርቅ ከሚረከብበት ከፍ ያለ ገንዘብ ለወርቅ አምራቾች ስለሚያቀርቡ በሕጋዊ መንገድ ወርቅ ገዝቶ ለባንክ ለማቅረብ መቸገራቸውን ይናገራሉ።

ከሰሞኑ ከማዕድን አምራቾችና ነጋዴዎች ጋር በአሶሳ ከተማ በተካሄደ ውይይት ላይ በዘርፉ የሚስተዋለው ሕገወጥነት ሰፊ በመሆኑ በመደበኛው የሕግ ሥርዓት ብቻ ይስተካከላል ተብሎ እንደማይታመን የጦር ኃይሎች ምክትል ኤታማዦር ሹም ጀኔራል አበባው ታደሰ መናገራቸውን ያስታወሰው መግለጫው ። ሕገወጥ እንቅስቃሴውን መስመር ለማስያዝ ካውንስሉ አስፈላጊውን እርምጃ ሁሉ እንዲወስድ በመንግሥት መታዘዙንም አስታውቀዋል። በዘርፉ የሚስተዋለው ሕገወጥነት ሰፊ መሆኑን በጥናት እንደለየ የጠቆመው የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎትም ሕግ የማስከበር እንቅስቃሴው ተጀመረ እንጂ አልተጠናቀቀም ብሏል።

የከበሩ ማዕድናትን በተለይም ወርቅን በሕገወጥ መንገድ ከሀገር በማስወጣት የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የሚጻረርና ከዘርፉ ሊገኝ የሚገባውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ በሚያሳጣ ድርጊት ለመከላከል የተቋቋመው በመከላከያ ሠራዊት የሚመራው ሀገር አቀፍ ካውንስልም፤ በዘርፉ የሚስተዋለውን ሕገወጥ ተግባር ከሥሩ ለመንቀል በሚያስችል ደረጃ ሥምሪት እየወሰደና ውጤቱን እየገመገመ ተፈፃሚ ማድረጉን እንደሚቀጥልና ይህንንም ለሕዝብ እንደሚሳውቅ አሳስቧል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleአቶ ይርጋ ሲሳይ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መሥተዳድር የሕዝብ ግንኙነትና የአደረጃጀት ዘርፍ አማካሪ ኾነው ተሾሙ።
Next articleበኩር ጋዜጣ በሰኔ 19/2015 ዓ.ም ዕትሟ