
ባሕር ዳር፡ ሕዳር 25/2012ዓ.ም (አብመድ) የኢትዮጵያ ብዙኃን መገናኛ ድርጅቶች የሀገር ውስጥ የእግር ኳስ ጨዋታን ለማሳደግ ከሰፈር የእግር ኳስ ጨዋታ መጀመር እንዳለባቸው የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት እና የሥነ ተግባቦት ትምህርት ክፍል መምህር እና ተመራማሪ ዶክተር ጀማል ሙሐመድ ተናገሩ፡፡
ዶክተር ጀማል ‹‹የሰፈር ኳስ መዘገብ አለበት›› ብለው የተናገሩት በወረታ ከተማ በአማራ ክልል ስፖርት ኮሚሽን አዘጋጅነት ለጋዜጠኞች፣ ለኮሙዩኒኬሽን ባለሙያዎች እና በስፖርቱ ዘርፍ ለሚመለከታቸው አካላት በተሠጠው የስፖርት ጋዜጠኝነት እና ተግባቦት ስልጠና ላይ ነው፡፡
በስልጠናው ዶክተር ጀማል እንደተናገሩት ኢትዮጵያ ብዙኃን መገናኛ ድርጅቶች ለአውሮፓ እግር ኳስ ትንታኔዎች ሰፊ ሽፋን ይሰጣሉ፤ ይህ ክፋት ባይሆንም የሀገራቸውን እግር ኳስ ለማሳደግ ከተፈለገ ግን ሜዳ ሳይኖራቸው በአስፓል ዳር የሚጫወጡ የሕጻናትን እንቅስቃሴም መዘገብ አለባቸው፡፡
‹‹የሰፈር ኳስ ጨዋታ ሲዘገብ የልጆቻቸውን እንቅስቃሴ በብዙኃን መገናኛ አውታሮች የሰሙ እና የተመለከቱ ወላጆችም ልጆቻቸውን ያበረታታሉ›› ብለዋል፡፡ ይህ ሲሆን ብቁ የኢትዮጵያ ልጆች እንደሚወጡና ኢትዮጵያ ከሆነ ሀገር ጋር ተጫውታ ተሸነፈች የሚለው ዜናም እንደሚቀንስ አመልክተዋል፡፡
‹‹ጋዜጠኞች የአንድ ድርጅት ተቀጣሪ ብቻ ሳይሆኑ ማኅበራዊ ኃላፊነትም አለባቸው›› ያሉት ዶክተር ጀማል እውነትን፣ ፍትሐዊነትን፣ ዓላማንና ግብን፣ ሚዛናዊነትን፣ ለኅሊና መኖርን እና መርህን መሠረት በማድረግ የኅብረተሰቡን መረጃ የማገኘት መብት ማስከበር እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
ስልጠናውን የተከታተሉት ተሳታፊዎችም የኢትዮጵያ የስፖርት ዘጋቢዎች የውጭ ዜና ማብዛት፣ በውስን የስፖርት ዓይቶች ማዘውተር፣ ለተወሰኑ አካባቢዎች ትኩረት መስጠት፣ ዘገባዎች ከተሠሩ በኋላ የት ደረሱ ብሎ አለመጠየቅ፣ የሚመለከታቸውን ባለሙያዎች አካትተው አለመሥራት፣ የስፖርት ፌዴሬሽኖች የተሥሩ ሥራዎችንና እቅዶችን በድረገጾቻቸው በየጊዜው ያለማውጣት እና የሥራ መሣሪያዎች እጥረት በስፖርት ጋዜጠኞች ላይ የታዩ ክፍተቶችመሆናቸው ተነስተዋል፡፡
የአማራ ክልል ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር ባዘዘው ጫኔ ‹‹ስፖርትን ለማሳደግ ብዙኃን መገናኛ ድርጅቶች ተኪ የላቸውም›› ብለዋል፡፡ አማራ ክልልን በተለያዩ የስፖርት ዘርፎች ውጤታማ ለማድረግ የመልክአ ምድር አቀማመጡ እና የአየር ንብረቱ ምቹ መሆኑን የተናገሩት ኮሚሽነሩ በክልል 22 የስፖርት ዓይነቶች ላይ እየተሠራ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡
የብዙኃን መገናኛ ድርጅቶች ዜጎች በስፖርቱ ዘርፍ ተሳታፊ እና ተጠቃሚ እንዲሆኑ፣ የስፖርታዊ ጨዋነት እንዲመጣ፣ የስፖርት ማዘወተሪያ ቦታዎች እንዲስፋፉ፣ ተተኪ ስፖርተኞች እንዲወጡ የሚያግዙ ዘገባዎችን እንዲሠሩም አሳስበዋል፡፡ ጋዜጠኞች የክልሉን የስፖርት መረጃዎች በቀላሉ እንዲያገኙ በስፖርት ኮሚሽኑ ማኅበራዊ ገፅ በኩል አስፈላጊ መረጃዎችን እንደሚለቅቅም አስታውቀዋል፡፡
ዘጋቢ፡- አዳሙ ሽባባው