ወልድያ ዩኒቨርሲቲ በጥገኛ ተዋህስያን ምክንያት በእንስሳቶች ላይ በሽታ እንዳይከሰት የቅድመ መከላከል ሕክምና እየሰጠ ነው።

51

ወልድያ: ሰኔ 18/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ወልድያ ዩኒቨርሲቲ ሕክምናውን የሰጠው በሰሜን ወሎ ዞን ጋዞ ወረዳ ነው፡፡ ከ14 ሺህ በላይ የዳልጋ፣ በግና ፍየሎችን የቅድመ መከላከል ሕክምና እንደሚሰጥም ተገልጿል፡፡

በዩኒቨርሲቲው የእንስሳት ሕክምና መምህር ሰለሞን ጸጋየ (ዶ.ር) ጥገኛ ተህዋሲያን በእንሰሳቶች ስጋ፣ ወተት፣ በቆዳና ሌጦ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚያሳድር አስረድተዋል፡፡

ይህንን ችግር ለመከላከል ዩኒቨርሲቲው በማኅበረሰብ ጉድኝት ዘርፍ የእንስሳት ደኅንነትና ሕክምና ፕሮጀክት ቀርጾ ቀድሞ ለመከላከል ሕክምና እየሰጠ ነው፡፡

የጋዞ ወረዳ እንስሳት ሀብት ልማት ተጠሪ ጽሕፈት ቤት እውነቱ የማታው በእንስሳት ሀብት ላይ የመኖና የዝርያ ችግሮች ቢኖሩም የእንስሳት በሽታ መከሰት አሳሳቢ ነው ብለዋል፡፡ በተለይ በጦርነቱ ምክንያት የእንስሳት ሕክምና ተቋማት በመውደማቸው ሕክምና ለመስጠት መቸገራቸውን አንስተዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው ወቅቱን የጠበቀ የቅድመ መከላከል ሕክምና መስጠቱ የአርሶ አደሮችን ተጠቃሚነት የሚያሳድግ በመኾኑ አመሥግነዋል።

ከሰብል ምርት የበለጠ በእንስሳት ሀብት እንደሚተዳደሩ የገለጡት በጋዞ ወረዳ የሻሪያገነት ቀበሌ ነዋሪ አቶ ሰማኝ ረዳ በበሽታ ምክንያት እንስሳትን ለማድለብ እንደሚቸገሩና አልፎ አልፎ ለሞት እንደሚዳረጉባቸውም ገልጸዋል ፡፡ ዩኒቨርሲቲው በነጻ እንስሳትን ስላከመላቸውም አመሥግነዋል።

በዞኑ 592 ሺህ 518 የዳልጋ ከብት፣ 757 ሺህ በግ፣ 550 ሺህ ፍየል እንደሚገኝ ከዞኑ እንስሳት ሀብት ልማት ተጠሪ ጽሕፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

ዘጋቢ፦ ባለ ዓለምየ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleከወልዲያ እስከ ጋሸና ያለው የአስፋልት መንገድ ብልሽት ነዋሪዎችን ለተራዘመ እንግልት እያጋለጠ መኾኑ ተገለጸ።
Next articleአቶ ይርጋ ሲሳይ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መሥተዳድር የሕዝብ ግንኙነትና የአደረጃጀት ዘርፍ አማካሪ ኾነው ተሾሙ።