ከወልዲያ እስከ ጋሸና ያለው የአስፋልት መንገድ ብልሽት ነዋሪዎችን ለተራዘመ እንግልት እያጋለጠ መኾኑ ተገለጸ።

89

ከወልዲያ እስከ ጋሸና ያለው የአስፋልት መንገድ ብልሽት ነዋሪዎችን ለተራዘመ እንግልት እያጋለጠ መኾኑ ተገለጸ።

👉 የኢትዮጵያ መንገዶች አሥተዳደር ጊዜያዊ ጥገና እያደረግሁ ነው፤ ዘላቂ መፍትሄውን ደግሞ በመጭው ዓመት እጀምራለሁ ብሏል።

ወልዲያ: ሰኔ 18/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ከወልዲያ እስከ ጋሸና ያለው አስፋልት መንገድ 108 ኪሎ ሜትር ርዝመት አለው። በሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ ለሚደረገው የሀገሪቱ ወጭ እና ገቢ ጭነት ኹነኛው መተላለፊያ መንገድ ነው። ከጅቡቲ በመነሳት በሚሌ ጭፍራ እና ወልዲያን አቋርጦ ወረታ ደረቅ ወደብ ላይ ገቢ ጭነት ለማራገፍ እና ወጭ ጭነት ለማንሳት አማራጭ የሌለው ብቸኛው መንገድ ይሄው ነው።

ይህ ለሀገር ኢኮኖሚ መሳለጥ ከፍተኛ ሚና ያለው መንገድ ከተበላሸ ቆይቷል። የወልዲያ -ጋሸና አስፋልት መንገድ በጥራት መጓደል ምክንያት በመበላሸቱ በአካባቢው ነዋሪዎች እና በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ጫና እያሳደረ እንደሚገኝ አሚኮ ኦንላይን በሐምሌ 2014 ዓ.ም ዘገባው ማስነበቡ ይታወሳል። በወቅቱ ስለጉዳዩ ጥያቄ ያቀረብንለት የኢትዮጵያ መንገዶች አሥተዳደር የመንገዱን ጥገና በቶሎ ጀምሮ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ ማቀዱን ገልጾልን ነበር። ይህ ዕቅድ ተግባራዊ ሳይኾን ዓመት ቢሞላውም የመንገዱ ብልሽት ግን ከበፊቱም ብሶበት ለነዋሪዎች እና ለሀገር ኢኮኖሚ ፈተና ኾኖ ቀጥሏል።

መንገዱ ከሚያቋርጣቸው ወረዳዎች መካከል ጋዞ ወረዳ አንዱ ነው። የወረዳው መንገድ እና ትራንስፖርት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አየነው ቢራራ በጋዞ ወረዳ ውስጥ እስካሁን ምንም ዓይነት ጥገና እንዳልተጀመረ ተናግረዋል። በመንገዱ ብልሽት ምክንያት የዞኑ ዋና ከተማ ወደኾነችው ወልዲያ ለመድረስ አስቸጋሪ ኾኗል ብለዋል። የመንገዱ ውጣ ውረድ የተሽከርካሪ ዕቃዎችን እየሰበረ እና እያበላሸ ነው። ይህንን ኪሳራ በመተካት ሰበብ ከልክ ያለፈ የትራንስፓርት ታሪፍ በተሳፋሪዎች ላይ እየተጫነ ነዋሪዎችን ለኢኮኖሚያዊ ችግር እያጋለጠ ስለመኾኑም አቶ አየነው ተናግረዋል።

መንገዱ በተለይም ከሰላም ስምምነቱ በኃላ እስከ ትግራይ ክልል ድረስ የሚመላለሱ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ተሽከርካሪዎች በችግር ውስጥ ኾኖም እያስተናገደ ነው። የተቆረጠውን መንገድ እና በየመሃሉ ያቆረውን ኩሬ መሰል ውኃ ለማለፍ የሚጥሩ ተሽከርካሪዎች እርስ በእርስ የመጋጨት እና ሌሎች አደጋዎችንም እያስተናገዱ ስለመኾኑ አቶ አየነው አስረድተዋል።

መንገዱ ለሀገር ኢኮኖሚ ጉልህ ሚና ያለው መኾኑን በመገንዘብ ዘላቂ ጥገና ተደርጎለት በጦርነት አዙሪት ውስጥ የቆየው የአካባቢው ነዋሪም እፎይታን ማግኘት አለበት ሲሉም ጠይቀዋል።

በኢትዮጵያ መንገዶች አሥተዳደር የኮምቦልቻ መንገድ ኔትወርክ እና ደኅንነት ማኔጅመንት ቅርንጫፍ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወይዘሮ ቃልኪዳን ተሾመ ከጦርነት በፊት የአማራ መንገድ ሥራዎች ድርጅት የጥገና ሥራውን በተቋራጭነት ይዞት እንደነበር ገልጸዋል። 1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ውል ተይዞለት ከባድ ጥገና እየተሠራ እንደነበርም አንስተዋል።

ወይዘሮ ቃልኪዳን የጥገና ሥራው በጦርነት ምክንያት እንደተቋረጠ ገልጸው ተቋራጩ ያቀረባቸው በርካታ ንብረቶች በመዘረፋቸው ተመልሶ በፍጥነት ወደ ሥራ ለመግባት አስቸጋሪ ነበር ብለዋል። አሁን ላይ ተቋራጩ ተመልሶ ወደ ጥገና ሥራው እንዲገባ የሚያስችል ንግግር እየተደረገ ስለመኾኑም አንስተዋል። የጊዜውን መራዘም ተከትሎ የሚያስፈልገው የዋጋ ለውጥ ተወስኖ በመጭው መስከረም 2016 ዓ.ም ዘላቂ ጥገና እንደሚጀመር ተናግረዋል።

ወይዘሮ ቃልኪዳን የመንገዱ አገልግሎት እንዳይቋረጥ የሚያስችል ጊዜያዊ ጥገና እየተካሄደ ስለመኾኑም አንስተዋል። ጊዜያዊ ጥገናው እስታይሽ ወረዳ ላይ ተጀምሮ ወደ ወልዲያ እየተሠራ መኾኑን ነው የተናገሩት። ከእስታይሽ እስከ ጋሸና ያለው ደግሞ በቀጣይነት ይጠገናል ብለዋል። ጊዜያዊ ጥገናው እስከ መጭው ሐምሌ አጋማሽ ድረስ ለማጠናቀቅ እየተሠራ ስለመኾኑም ወይዘሮ ቃልኪዳን ተናግረዋል።

ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ስልጠናው በአስፈጻሚ አካሉ ላይ የሚስተዋሉ የአሠራር መዛነፎችን መልክ በማስያዝ የተሻለ አመራር ለመፍጠር የሚያስችል ነው” የምዕራብ ጎጃም ዞን ብልጽግና
Next articleወልድያ ዩኒቨርሲቲ በጥገኛ ተዋህስያን ምክንያት በእንስሳቶች ላይ በሽታ እንዳይከሰት የቅድመ መከላከል ሕክምና እየሰጠ ነው።