
ፍኖተ ሰላም: ሰኔ 18/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በምዕራብ ጎጃም ዞን ከሁሉም ወረዳዎቸና ከተማ አሥተዳደሮች የተውጣጡ መካከለኛና ከፍተኛ አመራሮች የሚሳተፉበት “መፍጠንና መፍጠር የወል እውነቶችን የማጽናት የትግል ምዕራፍ “በሚል መሪ ሃሳብ ለሦስት ቀናት የሚቆይ ስልጠና መካሄድ ጀምሯል።
የምዕራብ ጎጃም ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አለባቸው ገነቱ የሚስተዋሉ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉድለቶችን ለማረምና አሁናዊ ሁኔታዎችን በመረዳት ላይ የተመሠረተ ጠንካራ አመራር ሰጪነትን በዞኑ ለማረጋገጥ ስልጠናው አቅም የሚፈጥር ነው ብለዋል።
በመኾኑም ከተናጠላዊ ፍላጎትና ስኬት ባሻገር የጋራ ጥቅምና ፍላጎቶች በትክክለኛ አካሄድ አንዲመጣና አብሮነት እንዲጸና ወቅቱ የሚጠይቀው የአመራር ስብዕና በመኾኑ ይህንን ተረድቶ ወደ ተግባር የሚቀይር አመራር መፍጠር ዋናው ጉዳይ ነውም ነው ያሉት።
ከስልጠናው በኋላም ሁለንተናዊ የለውጥ አቅሞችን በመጠቀም የኑሮ ውድነትና ሥራ አጥነትን መቀነስ፣ ማኅበራዊ ጉድለቶችን ማረምና ሁለንተናዊ የሕዝብ ችግሮችን መፍታት የአመራሩ ቀዳሚ ተግባር ይኾናል ብለዋል።
ስልጠናው “በአስፈጻሚ አካሉ ላይ የሚስተዋሉ የአሠራር መዛነፎችን መልክ በማስያዝ በንድፈ ሃሳባዊ መረዳትም ኾነ በተግባር አፈጻጸም የተሻለ አመራር ለመፍጠር የሚያስችል ነው” ያሉት ደግሞ የምዕራብ ጎጃም ዞን ዋና አሥተዳዳሪ መልካሙ ተሾመ ናቸው።
ለአመራሩ ተጨማሪ አቅም በመፍጠር የሕዝብን ሁለንተናዊ ችግሮች ለመፍታትና ዓለማቀፋዊ ሁኔታዎችን ለመረዳት ያግዛል ብለዋል።
በመድረኩም የእስከዛሬውን የለውጥ ጉዞ መገምገም እና ጥንካሬዎችን፣ ዕድሎችንና ስጋቶችን በዝርዝር በመለየት ወቅቱ የሚፈልገውን የአመራር ቁመና መላበስ የሚያስችል ውይይት ይደረጋል ነው ያሉት።
ስልጠናው ለሦስት ተከታታይ ቀናት የሚቆይ ሲኾን ከሁሉም ወረዳዎችና ከተማ አሥተዳደሮች እንዲሁም ከዞን የሥራ ኀላፊዎች የተውጣጡ ከ650 በላይ መካከለኛና ከፍተኛ አመራሮች እንደሚሳተፉ ለማወቅ ተችሏል።
ዘጋቢ :- ዘመኑ ይርጋ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!