
👉 ለማኅበራት የተሠጡ ቦታዎች ላይ የህንፃ ከፍታው G+1 እና በላይ እንደየ ማኅበሩ ምርጫ እንዲሆን ተወስኗል።
ባሕር ዳር: ሰኔ 18/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር) የቤት ማኅበራት የማጣራት ሂደትን አስመልክቶ ዛሬ መግለጫ ሰጥተዋል።
ዶክተር ድረስ በቀጣይ ቀናት በማጣራት ሂደቱ ችግር ለሌለባቸው ማኅበራትና የማኅበር አባላት ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ የግንባታ ፍቃድ እንዲሠጣቸው መወሰኑን አብራርተዋል። የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን መምሪያው በሚያወጣው ማስታወቂያ መሠረት የሚስተናገዱ ይሆናል ብለዋል።
ከተማ አስተዳደሩ በማኅበር ተደራጅተው ቦታ ለማግኘት ይጠባበቁ ለነበሩ ዜጎች ልዩ ትኩረት በመስጠት ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ መልስ ለመስጠት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ከንቲባው ገልፀዋል ።
የማደራጀት ሂደቱ ችግር እንዳለበት የኅብረተሠቡን ጥቆማ መሻ በማድረግ ከተማ አስተዳደሩ የተለያዩ አጣሪ ኮሚቴዎችን በማደራጀት ሲሠራ መቆየቱን ገልፀዋል።
ችግሩን ለመፍታት ሁለት አጣሪ ኮሚቴዎችን በማዋቀር ወደ ስራ ማስገባት መቻሉን ነው ከንቲባው የገለፁት።
የመጀመሪያው አጣሪ ኮሚቴ ስድስት አባላት ያሉት ሲሆን የተሠጠው ተልዕኮ መሬታቸው ከተወሠደባቸውና ተነሽ ከሆኑ የአርሶ አደር ልጆች ጋር የቀረበውን ጥቆማ እንዲያጣራ የተደረገ ነው።
ሁለተኛው አጣሪ ኮሚቴ አራት አባላት ያሉት ሲሆን ተልዕኮው በማኅበር ተደራጅተው የመኖሪያ ቤት መሥሪያ ቦታ ከደረሳቸው የኅብረተሠብ ክፍሎች ጋር በተያያዘ የሚነሡ ጥቆማዎችን የማጣራት ተግባር ይዞ ሲሠራ ቆይቷል ብለዋል።
በአጣሪ ኮሚቴው የተገኘውን ውጤት በተመለከተ ዶክተር ድረስ እንደገለፁት ከአርሶ አደር ልጆች ጋር በተያያዘ በዘንዘልማና በመሸንቲ መሬታቸው ለልማት ከተወሰደባቸው አርሶ አደሮች ልጆች ጋር በተያያዘ አጣሪ ኮሚቴው ከደረሠው ጥቆማ በመነሳት ባደረገው ጥቆማ መሰረት የሚከተሉትን ማረጋገጥ ተችሏል። የአርሶ አደር ልጆች ያልሆኑ፣ እድሜያቸው ያልደረሱ፣ ከቤተሠብ ወጥቶ የራሡን ኑሮ እየመራ ያለ፣ መሬታቸው ያልተካለለባቸው አርሶ አደሮች ልጆች በአጠቃላይ ከዘንዘልማ 648፣ ከመሸንቲ 107 በድምሩ 715 ግለሰቦች የአርሶ አደር ልጆች ነን በሚል አላግባብ የመኖሪያ ቤት መሥሪያ ቦታ እንዳያገኙ፣ ግለሰቦች ያላግባብ እንዳይወስዱ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።
ከሁለተኛው አጣሪ ኮሚቴ አኳያ ጠቅላላ ቦታ ካገኙት 820 ማኅበራት ውስጥ 520 ማኅበራት ወይም 10 ሺ 628 ተመርምረው 804 ግለሰቦች ከአሠራር ውጭ ተደራጅተው ተገኝተዋል።
በአጣሪ ኮሚቴው የተገኘው ያሠራር ክፍትተና ችግር ውስጥ በባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ ሳይሆኑ ነዋሪ እንደሆኑ አስመስለው ተደራጅተው መገኘት፣ በመመሪያው መሰረት በከተማው ለሁለት ተከታታይ ዓመታት ሳይኖሩ ተደራጅተው መገኘት፣ ከማህበሩ ፋይል ውስጥ ስማቸው ሳይኖር ቦታ የወሠዱ ግለሰቦች መገኘት፣ ቀደመው ተደራጅተው ነገር ግን ቦታ ሳይደርሳቸው ህይወታቸው ባለፋ ሠወች ስም ቦታ ተሠጥቶ መገኘት ፣ የተጭበረበረ የስራ ግብርና የስራ ልምድ ማስረጃ በማቅረብ ተደራጅቶ መገኘት፣ ባልና ሚስት ሁነው በየግላቸው ተደራጅተው መገኘት፣ ከባሕር ዳር ውጭ ባሉ የክልሉ ከተሞች ቤት ያላቸውና በድጋሚ እዚህ ተደራጅተው መገኘት እና ሲደረጁ ግልፅ የሆነ የሥራ ዘርፍ አስቀምጠው ነገር ግን አሁን ላይ ሲጠየቁ ያንን የሚያስረዳ መረጃ አለማቅረብ ሲሆን በድምሩ በዚህ ችግር ውስጥ 804 ሰወች ተገኝተዋል።
ዶክተር ድረስ በቀጣይ ቀናት በማጣራት ሂደቱ ችግር ለሌለባቸው ማኅበራትና የማኅበር አባላት ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ የግንባታ ፍቃድ እንዲሠጣቸው መወሰኑን አብራርተዋል። የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን መምሪያው በሚያወጣው ማስታወቂያ መሠረት የሚስተናገዱ ይሆናል ብለዋል።
ለማኅበራት የተሠጡ ቦታዎች ላይ የህንፃ ከፍታው G+1 እና በላይ እንደየ ማኅበሩ ምርጫ እንዲሆን መወሠኑን አሳውቀዋል።
ዶክተር ድረስ ለዚህ ውጤት መገኘትና ብልሹ አሠራርን በመታገል፣ ጥቆማ በመስጠት አስተዋጽኦ ላደረጉ የከተማዋ ነዋሪዎች ፣ የማጣራት ሂደቱን በትዕግስት ሲጠባበቁ ለነበሩና ከከተማ አሥተዳደሩ ጋር በቅርበት አብረው ሲሠሩ ለነበሩ የማኅበር አባላትና የኮሚቴ አባላትን አመስግነዋል።
በማጣራት ሂደቱ ቅሬታ የሚኖራቸው ግለሰቦች ካሉ የከተማ አሥተዳደሩ የቅሬታ ማስተናገጃ ስርዓት ያዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህ ጥፋት ውስጥ ገብተው የተገኙ አካላትን በሂደት አስተማሪ የሆነ እርምጃ ለመውሰድ ከተማ አሥተዳደሩ የሚሠራ መኾኑን ዶክተር ድረስ መግለጻቸውን ከከተማ አሥተዳደሩ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!