
ባሕር ዳር: ሰኔ 18/2015 ዓ.ም (አሚኮ) አንድ ማንነት፣ አንድ እውነት፣ ብርቱ ጀግንነት፣ አትንኩኝ ባይነት፣ መከራ የማያስደነግጠው፣ ጨለማ ውጦ የማያስቀረው፣ እሾህና አሜኬላ የማያስቆመው፣ የጥይት አረር የማይበግረው ልበ ሙሉነት አላቸው፡፡ ማንነታቸው አይለወጥም፣ እውነታቸው አይደበዝዝም፣ ታሪካቸው አይዳፈንም፣ በመከራዎች ውስጥ ያበራል፣ በጨለማ ውስጥ በአሻገር ይታይል እንጂ፡፡ የማይለወጥ ማንነታቸውን፣ የማይደፈር ጀግንነታቸውን ችሎ የሚገፋው፣ ኾኖለት የሚያጠፋው የለም፡፡ ሕያው ኾኖ ይኖራል፣ የዘመን ፀሐይ ኾኖ ያበራል እንጂ፡፡
ግፍ ሲበዛባቸው ይጠነክራሉ፣ መከራው ሲጸናባቸው የባሰ አንድ ይኾናሉ፣ ከጀግንነት ላይ ጀግንነት፣ ከጀብዱ ላይ ጀብዱ ይደራርባሉ፡፡ ለዓመታት በጸና ጀግንነት ታግለዋል፣ ለማንነት እና ለጸናች እውነት አያሌ መስዋዕትነቶችን ከፍለዋል፡፡ የግፍ ጽዋን ተቀብለዋል፡፡ የመከራ ዶፍ እየወረደባቸው፣ የሞት አውታር በፊትና በኋላቸው፣ በቀኝና በግራቸው እየተመላለሰባቸው እነርሱ ስለ እውነት፣ የእውነት፣ በእውነት ታግለዋል፣ እንደ ዓለት ጠንክረዋል፡፡
ከልባቸው ላይ የታጠቁ፣ የነገውን ዛሬ ላይ በጥበብ የሚያውቁ፣ ዛሬ ላይ ለነገ መልካም ታሪክ የሚሰንቁ፣ ተስፋን እና ጀግንነትን፣ ድፈረትና ልበ ሙሉነትን የሚያስታጥቁ ጀግኖችና ብልኾች ናቸው፡፡ ለወዳጃቸው ማርና ወተት ያቀርባሉ፣ ለጠላታቸው የጥይት አረር ያስጎነጫሉ፡፡ ለአንዲት ሠንደቅ ክብር፣ ለአንዲት ሀገር ፍቅር ተዋድቀዋል፣ ለሕዝብ ክብር ደም አፍስሰዋል፣ አጥንት ከስክሰዋል፣ ሕይዎት ገብረዋል፡፡
ጠላት ድንበር እጥሳለሁ፣ ሠንደቅ አረክሳለሁ ባለ ጊዜ ሁሉ ጠመንጃቸውን ወልውለው፣ ሳንጃቸውን ስለው በረሃ ይወርዳሉ፡፡ ረሃብና ጥሙን ችለው፣ አሜኬላውን እና መከራውን ረስተው፣ ምሽግ ውለው፣ ምሽግ አድረው፣ የአንዲት ሀገርን ክብር ያስከብራሉ፡፡ መሠረታቸው እውነት፣ መገለጫቸው ጀግንነት ነውና፡፡
ስማቸው ተደጋግሞ ይጠራል፣ ጠለምት፣ ጠለምት ይባላል፡፡ ጠለምት ፈሪ እንዳሻው አይረማመድበትም፣ ሰላቶና ባንዳ አይኖርበትም፣ በጀግኖች ምድር የሚኖረው ጀግና ብቻ ነው እንጂ፡፡ ምድሩ ጀግንነት እንዲሠራበት፣ ጀግኖች እንዲኖሩበት፣ ልበ ሙሉዎች እንዲመላለሱበት፣ ጽኑዎች በኩራት እንዲታዩበት የተፈጠረ ይመስላል፡፡ ፈጣሪ አስውቦ የሠራው፣ ግርማና መወደድን የሰጠው ነው፡፡ ጠለምትና ወልቃይት ስማቸው ከፍ ብሎ ተጠርቷል፡፡ ስለ ስማቸው እና ስለ እውነታቸው መስዋዕትነት ተከፍሎባቸዋል፡፡ በእነርሱ ስም የተነሳ ጀግና ሕዝብ ሥርዓት እስከመቀየር ደርሷል፡፡ ክፉን ወንበር ገርስሷል፡፡ ነጻነትን እና ማንነትን አስመልሷል፡፡ ጀግና ተወልዶ ጀግና የሚያድግባቸው እነዚህ ስመ ጥር እና ታሪካዊ ስፍራዎች አያሌ የታሪክ ገፆች አሏቸው፡፡
የጠለምት ጀግኖች ማንነታቸው፣ ታሪካቸው፣ ሥነ ልቦናቸው ሁሉም ነገራቸው ከጎንደር ጋር ነው፡፡ የቀድሞው የስሜን በጌምድር ጠቅላይ ግዛት አንድ አካል ነው ጠለምት፡፡ ጠለምትን ከጃናሞራ፣ ከበየዳ፣ ከዳባትና ከደባርቅ፣ ከጃኒ ፈንቃራ፣ ከጃኖራና ከቆላ ወገራ፣ ከአርማጭሆ፣ ከመተማና ከቋራ፣ ከደንቢያና አለፋ፣ ከደራና ከፎገራ፣ ከወልቃይት ጠገዴና ከሁመራ፣ ከእብናት ከበለሳ፣ ከከምከም ከቃሮዳ፣ ከጋይንት፣ ከእስቴ፣ ከስማዳ በጥቅሉ ከጎንደር አማራ ሕዝብ መለየት አይቻልም፡፡ ስለምን ከተባለ በማንነቱ አንድ ሕዝብ ነውና፡፡
“አምላክ ሰው በሰው በሚያደርገው የግፍ ሥራ ተጋፊነት ሰውን ጨርሶ ከሀገሩ ላይ ሊያጠፋው አይፈቅድም፣ እንዱን ሲገድል አንዱን ለምስክርነት ያቆመዋል፡፡ ከቶ በሰው ላይ የሚመጣው ቁጣ ሁሉ ታዛቢ ሳይቀመጥ ምስክር ሳይዘጋጅለት እንዲያው ድምስስ አድርጎ አያጠፋውም” እንዳሉ ግርማ ታፈረ ክፉዎች መከራዎችን ሊያበዙ ይችሉ ይኾናል፡፡ ነገር ግን እውነትን እና ማንነትን ፈጽሞ ማጥፋት አይቻላቸውም፡፡ ታሪክ ነጋሪ እውነት መስካሪ በምድሪቷ አይጠፋም፡፡
እኔም አንድ ታሪክ ነጋሪ እና እውነት መስካሪ ሰው ጋር ተገናኝቻለሁ፡፡ ስለሺ ንጉሤ ደስታ ይባላሉ፡፡ የማይጠብሪ ከተማ ተዋላጅ ናቸው፡፡ አሁን ኑሯቸውን በአሜሪካ ካሊፎርንያ አድርገዋል፡፡ ስማቸውን እና የትውልድ ሥፍራቸውን በጠየኳቸው ጊዜ “ ስለሺ ንጉሤ ደስታ እባላለሁ፡፡ የትውልድ ቦታዬ በጎንደር ክፍለ ሀገር፣ በስሜን አውራጃ፣ ማይጠብሪ ከተማ ነው” ነበር ያሉኝ፡፡ በአሁኑ አጠራር በአማራ ክልል በሰሜን ጎንደር ዞን በጠለምት ወረዳ ማይጠብሪ ከተማ ማለት ነው።
ጠለምት በታሪክ ከጎንደር ክፍለ ሀገር ተነጥሎ አያውቅም፣ ሊነጠልም አይችልም ይላሉ፡፡
ስለ ጠለምት ታሪክ ሲነግሩኝ ቀደም ያለውን ሌላውን ታሪክ እንኳን ብንተወው በእኔም፣ በአባቴም፣ በአያቴም በቅድመ አያቴም እድሜ ጠለምት የሚተዳደረው በጎንደር ክፍለ ሀገር እንጂ በማንም አይደለም፤ በትንሹ ከእኔ እስከ አያቴ ድረስ ያለውን እድሜ ብንቆጥር ሁለት መቶ ዓመታት በላይ ይኾናል፣ በዚህ ሁሉ ዘመን ታዲያ ጠለምት የሚተዳደረው በጎንደር ክፍለ ሀገር ነው፣ ጠለምት ማንነቱ አማራ፣ ስነልቦናው የአማራ፣ ቋንቋው አማርኛ የኾነ ነውም ብለውኛል፡፡
ለትግራይ አዋሳኝ በመኾኑ ከዋናው ቋንቋ አማርኛ በተጨማሪ የአካባቢው ሕዝብ ትግርኛም እንደሚናገር የነገሩኝ ጋሽ ስለሺ ያ ግን የኾነው በጉርብትና እንጂ ማንነቱ ትግሬ ስለኾነ አይደለም ነው ያሉት፡፡
ጠለምት ከቀደመው ዘመን ጀምሮ የስሜን በጌምድር ወይም የጎንደር ክፍለ ሀገር አካል የነበረ እንጂ በታሪክ በትግራይ ክፍለ ሀገር ተዳድሮ የማያውቅ፣ ይህ ብቻ አይደለም ከትግራይ የመጣ ሰውም አሥተዳድሮት የማያውቅ እንደኾነም ነግረውኛል፡፡ ተከዜ ሕያው ምስክር፣ ወሰን እና ድንበር የኾነ ነው፣ ስሜን በጌምድር እና ትግራይ ክፍለ ሀገር የሚዋሰኑት ተከዜ ላይ ነው ይላሉ ጋሽ ስለሺ፡፡ ማይጠብሪ ከተማን ከቆረቆሩ ሰዎች መካከል የእርሳቸው ቤተሰቦች እንደሚገኙበትም ነግረውኛል፡፡
ከትግራይ ክፍለ ሀገር የሚመጡ ሰዎች ለእርሻ ለሥራ ይመጣሉ፣ ሲሠሩ ከርመው ወደ መጡበት ይመለሳሉ፣ ጠለምት ግን በትግራይ ሥር ተዳድሮ አያውቅም ነው ያሉኝ፡፡ ጠለምት ጀግና እና ኩሩ ባላባቶች የነበሩበት፣ ያሉበት፣ በኢጣልያ ወረራ ጊዜ ለሀገር መስዋዕት የከፈሉ ጀግኖች አርበኞች የነበሩበት አካባቢ መኾኑንም ነግረውኛል፡፡ ገሪማ ታፈረም ጎንደሬ በጋሻው በተሰኘው መጽሐፋቸው ጠለምት ላይ የስሜን በጌምድር አርበኞች ያደረጉትን ተጋድሎ ጽፈዋል፡፡ አድ ወሰኔ፣ ግልቤና፣ ጭንፈራ እና ሌሎች የስሜን በጌምድር ጠቅላይ ግዛት የስሜን አውራጃ የጠለምት አካባቢዎች አያሌ ጦርነቶች የተካሄዱባቸው ናቸው፡፡ የጠለምት ጀግኖች የኢጣልያን ወራሪ ሠራዊት በአንድነት እና በፍጹም ጀግንነት ድል እንደመቱትም ገሪማ ታፈረ ጽፈዋል፡፡
ጠለምት በትግራይ ነው ማለት ከምኞት የዘለለ ምንም አይነት እውነት የለውም ነው ያሉት ጋሽ ስለሺ፡፡ የዋልድባን ታሪክ ብቻ ለጠየቀ ጠለምት የስሜን በጌምድር ጠቅላይ ግዛት አንድ አካል መሆኑን ያውቃል፣ ይረዳልም ብለውኛል፡፡ ጠለምትን ያለ ታሪኩ፣ ያለ ሥነ ልቦናው እና ያለ ባሕሉ ወደ ትግራይ ለመውሰድ የከጀሉ ሰዎች ታሪክ አዋቂዎችን፣ እውነት ተናገሪዎችን ሲገድሉ መኖራቸውንም ነግረውኛል፡፡
የጠለምት ማንነት አንድ፣ እውነቱ አንድ የኾነ፣ የአማራ ማንነት ያለው፣ ጠለምት ትግራይ ኾኖ የማያውቅ ወደፊትም የማይኾን ነው ብለውኛል፡፡ ጠለምትን ታላቋን ትግራይን ለመመስረት ለነበራቸው ራዕይ የወሰዱት እንጂ አንድም የታሪክ ማስረጃ ማቅረብ የማይችሉ፣ ከተከዜ ተሻግረው የማያውቁ ናቸውም ብለውኛል፡፡ ታሪክን የሚያበላሹ፣ የተዋለደውን እና በጋራ የኖረውን ሕዝብ እንዲጣላ ያደረጉና የሚያደርጉ ናቸውም ብለዋቸዋል፡፡ የአካባቢውን ታሪክ ለማጥፋት እና ማንነቱን ለመቀየር ታሪክ አዋቂዎችን በግፍ መግደላቸውን፣ ማሳደዳቸውን፣ ባላባቶችን ፣ የሃይማኖት አባቶችን፣ ማንነቴን አትንኩብኝ ያላቸውን ሁሉ ለግፍ ዳርገዋል፡፡ የጠለምት ሕዝብ ግን ለዓመታት በግፍ ውስጥ ኾኖ ለማንነቱ ታግሏል፣ ማንነቱንም አስመልሷል ነው ያሉኝ፡፡
ጠለምትን በማታለል እና በመደለል ማንነቱን ማስቀየር አይቻልም፣ የፈለገውን ያክል መከራው ቢበዛበት ማንነቱን አሳልፎ አይሰጥም፣ ከከፍታውም አይወርድም ይላሉ፡፡ የትግራይ ታጣቂዎች ከመጡበት ጊዜ ጀምሮ የጠለምት ጀግኖች ለማንነታቸው ሲዋደቁ እንደኖሩም ያስታውሳሉ፡፡
አጥፊዎች ለአጥፊነታቸው በነጻው ሕዝብ ላይ የባርነት ቀንበር ሊጭኑ ባጠመዱ ጊዜ በተፈጥሮ ቀንድ አጥማጁን ወግተው ቢዘርሩት ለመከላከል የፈጠረው የተፈጥሮ ጀግንነት ነው እንደተባለ ጀግኖቹ በነጻነታቸው የመጣውን ጥለውታል፡፡ ለነጻነቱ እና ለማንነቱ ያልተሰቃየ፣ መከራን ያልተቀበለ ታሪክ ማውረስና መውረስ አይቻለውም፡፡ የጠለምት ጀግኖች ግን ታሪክን በመስዋዕትነት ወርሰዋል፣ አውርሰዋል፡፡
በታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!