
ባሕር ዳር: ሰኔ 17/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር በድሃና ወረዳ በጭላ ቀበሌ ከ4 በላይ ቀበሌዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ለመጀመሪያ ጊዜ የእግረኛ ተንጠልጣይ ድልድይ በክልሉ መንግሥትና ሄልቫተስ ስዊዝ በተሰኘ ግብረሰናይ ድርጅት ከ5 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ተሠርቶ ተመርቋል።
ከቀበሌ 018 ወደ ቀበሌ 022 ለገበያ ሲሻገሩ ያገኘናቸው የአካባቢው ነዋሪ አቶ ወዳጄ አማረ እና አቶ ጊዜው በሬ ከአሁን በፊት በክረምት ወራት ተንጠልጣይ ድልድዩ የተሠራበትን ወንዝ ለመሻገር ይቸገሩና በርካታ እንግልት እንደሚደርስባቸው ገልጸው ዛሬ ተንጠልጣይ ድልድዩ በመሠራቱ መደሰታቸውን ነግረውናል።
የድሃና ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኀላፊና ምክትል አሥተዳዳሪ ዘነበ ማሞ ተንጠልጣይ ድልድዩ እንዲሠራ ባለፉት ዓመታት ሲጠይቁ መቆየታቸውን ገልጸው ዛሬ ጥያቄው ምላሽ አግኝቷል ብለዋል። በዚህም ክረምት በጎርፍ ምክንያት በእንስሳትና በሰው ላይ ይደርስ የነበረውን ጉዳት ያስቀረዋል ነው ያሉት።
የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር መንገድ መምሪያ ኀላፊ ሰሎሞን እሸቱ እንዳሉት ኪታራ ተንጠልጣይ ድልድይ 65 ሜትር ርዝመት ያለው ሲኾን ከ5 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጎበታል ብለዋል።
ከወጣው ወጪ ውስጥ የክልሉ መንግሥት 80 በመቶ እና ሄልቫተስ ስዊስ የተሰኘው ግብረሰናይ ድርጅት 20 በመቶ ሸፍነዋል ነው ያሉት።
በሄልባተስ ስዊስ የተንጠልጣይ ድልድዮች ናሽናል ኮርድኔተር ወይዘሮ ፀሐይ ፀጋዬ ባለፉት 20 ዓመታት ውስጥ ድርጅቱ በሀገር አቀፍ ደረጃ 115 ተንጠልጣይ ድልድዮችን የሠራ ሲኾን ከእነዚህ ውስጥ 35 በአማራ ክልል ነው ብለዋል።
ወይዘሮ ፀሐይ በዘንድሮው ዓመት በአማራ ክልል 17 ተንጠልጣይ ድልድዮች እየተሠሩ መኾኑን ነው የተናገሩት።
የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ ስቡህ ገበያው (ዶ.ር) የተሠራው የእግረኛ ተንጠልጣይ ድልድይ ለማኅበረሰቡ ክረምት ሲመጣ የነበረውን ሰቀቀን ይቀንሳል ነው ያሉት።
ዘጋቢ፦ ሰሎሞን ደሴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!