ዓለማቀፍ የምግብ ድጋፍ የተቋረጠበትን ምክንያት ለይቶ ሕጋዊ እርምጃ ለመውሰድ ከረጅ ድርጅቶች ጋር የጋራ ኮሚቴ ተቋቁሞ እየሠራ መኾኑን የኢትዮጵያ መንግስት አስታወቀ።

44

ባሕር ዳር: ሰኔ 17/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በቅርቡ የአለም ምግብ ፕሮግራምና የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት USAID ለኢትዮጵያ የሚያቀርቡትን ሰብአዊ ድጋፍ ለጊዜው መግታታቸውን ማሳወቃቸው ይታወሳል።

ከዚሁ ጋር በተገናኘ መንግስት ከአጋር አካላቱ ጋር በጋራ በመሆን የአሠራር ክፍተት አለባቸው የተባሉትን ለመፈተሽ፤ ማሻሻያ ለማድረግና ህገወጥ ተግባራትም ተፈፅመው ከተገኙ አጣርቶ ህጋዊ እርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ መሆኑን አሳውቋል።

ይህንንም ተከትሎ በአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን መሪነት ከጉዳዩ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸው ተቋማት ተወካዮችንና የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት USAID ባለሙያዎችን ያካተተ የጋራ የቴክኒክ ኮሚቴ ተዋቅሮ በዘርፉ የአሠራር ማሻሻያ የሚያስፈልጋቸውን መለየትና የመፍትሄ ሃሳቦችንም ማመላከት ጀምሯል።

አስቸኳይ ሰብአዊ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች ተገቢው ድጋፍ እንዲደርሳቸው ማድረግ መንግስት ከፍተኛ ትኩረት የሰጠው አጀንዳ መሆኑ ይታወቃል። በዚህ ሂደት ውስጥ የህግ የበላይነትንም ለማስፈን ህገወጥ ድርጊት ውስጥ ተሳትፈው የተገኙ ግለሰቦችን ለህግ ሲያቀርብና ሰፊ ክትትልም ሲያደረግ ቆይቷል። መንግስት ተጠያቂነትን የማስፈን ተግባሩን አሁንም በሰፊው አጠናክሮ ይቀጥላል።

የጋራ ኮሚቴው በአስቸኳይ ሰብአዊ ድጋፍ፤ በሴፍቲኔት መርሃ ግብርና በስደተኞች የሰብአዊ ድጋፍ አቅርቦትና ስርጭት ላይ ነው ትኩረቱን አድርጎ እየመከረ የሚገኘው።

እስካሁንም መልካም ውጤቶች የተገኘባቸው ምክክሮችን አካሂዷል።

ከመንግስትና ከአጋር አካላቱ የተውጣጡ የሥራ ኀላፊዎችና ባለሙያዎች እየተሳተፉበት የሚገኘው የጋራ የቴክኒክ ኮሚቴ የደረሰበትን ውጤት በቅርቡ ይፋ እንደሚደረግ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት
ዛሬ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል ።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየጂቡቲ መንግስት የሀገሪቱን የፖሊስ የክብር ኒሻን ለፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ሸለመ ።
Next articleከ5 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተሠራው የእግረኛ ተንጠልጣይ ድልድይ ለአግልግሎት ክፍት ኾነ።