
👉 እስከ ታኅሳስ/2016 ዓ.ም ግንባታው ሙሉ በሙሉ ይጠናቀቃል ተብሏል።
ባሕር ዳር: ሰኔ 17/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በደቡብ ጎንደር ዞን እስቴ – ስማዳ አስፋልት ኮንክሪት መንገድ ግንባታ በፍፃሜ ምዕራፍ ላይ እንደሚገኝ የፕሮጀክት የተቆጣጣሪ መሀንዲስ ኀላፊ አሰፋ አበበ ነግረውናል። ኀላፊው እንዳሉት የመንገድ ፕሮጀክቱ 50 ነጥብ 4 ኪሎ ሜትር ነው። ግንባታው እስቴን ከአማራ ሳይንት ጋር ለማገናኘት አላማ ያደረገ ነው። ግንባታውን ዓለም አቀፉ ቻይና ኮሙኒኬሽን ኮንስትራክሽን ካምፓኒ CCCC እያከናወነው ይገኛል። በፌደራል መንግሥት ከ1 ቢሊዮን 540 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት ተመድቦለታል።
ግንባታው የካቲት 2011 ዓ.ም ተጀምሮ በሦስት ዓመት ለማጠናቀቅ ቢታቀድም በወሰን ማስከበር፣ በጦርነት፣ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እና በመጀመሪያ ለመሥራት የታሰበውን ሁለተኛ ደረጃ አስፋልት ወደ አስፋልት ኮንክሪት ለማሳደግ የወሰደውን ጊዜ ለማካካስ ተጨማሪ 421 ቀን ተሰጥቶ በመከናወን ላይ ይገኛል።
አሁን ላይ ከአጠቃላይ የግንባታ ሥራው 88 በመቶ ተከናውኗል። 47 ኪሎ ሜትሩን ደግሞ አስፋልት ማልበስ ተችሏል። እስከ ሰኔ 30/2015 ዓ.ም ጊዜያዊ ርክክብ እንደሚደረግም ተገለጿል።
በዚህ ወቅት ቀሪ 3 ነጥብ 4 ኪሎ ሜትር በከተማ ክልል ላይ ከወሰን ማስከበር ጋር ተያይዞ የተፈጠረው ችግር መፈታቱን ገልጸዋል። እስከ ታኅሳስ/2016 ዓ.ም ደግሞ ሥራው ሙሉ በሙሉ ይጠናቀቃል ተብሏል። መንገዱ አሁን ላይ የትራንስፖርት አገልግሎት እየሠጠ መኾኑን አንስተዋል።
የመንገዱ ሥራው እንዲፋጠን የአካባቢው ማኅበረሰብ ድጋፍ ከፍተኛ እንደነበር ነው ተቆጣጣሪ መሀንዲሱ የገለጹት።
ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ በሥፍራው የሚገኙትን ትንንሽ መንደሮች ደረጃውን በጠበቀ መንገድ በማገናኘት ወደ ከተማ የሚያድጉበትን ዕድል ይፈጥራል፡፡ የማኅበረሰቡን የማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መስተጋብሮችም ያጠናክራል፡፡
በአካባቢው በስፋት የሚመረቱትን እንደ ጤፍ፣ ስንዴ፣ ገብስ፣ ሽንብራ የመሳሰሉ የግብርና ምርቶችን በፍጥነት ወደ ገበያ ለማድረስ ያስችላል፡፡
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!