
ባሕር ዳር: ሰኔ 17/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
ሚኒስትር ዴኤታዋ በመግለጫቸው ኢትዮጵያ እምቅ የቱሪዝም ሀብቷን ለማስተዋወቅ የቱሪዝም አውደ ርእይ ማዘጋጀቷን አስታውቀዋል፡፡ የቱሪዝም አውደ ርእይው በአዲስ አበባ እንደሚካሄድም ተመላክቷል፡፡
የቱሪዝም ዘርፉ ከቀዳሚ የልማት ዘርፎች መካከል አንዱ እንደኾነ ያነሱት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ በኢትዮጵያ ያለውን እምቅ የቱሪዝም ሀብት ለማሳየት፣ የባሕል፣ የታሪክና ተፈጥሯዊ የቱሪዝም ሀብቶችን ለማስተዋወቅ የሚያስችል አውደ ርእይ ተዘጋጅቷል ነው ያሉት፡፡
የቱሪዝም ሀብቶቹ ለጎብኚዎቹ ምቹ ኾነው መዘጋጀት እንደሚገባቸውም ገልጸዋል፡፡ የቱሪዝም አገልግሎት ሰጪዎችም በቁጥርና በጥራት ከፍ ማለት አለባቸው ነው ያሉት፡፡ ኢትዮጵያ ከቱሪዝም ማግኘት የሚገባትን ገቢ ለማሻሻል ያለመ አውደ ርእይ እንደሚካሄድ ነው የተናገሩት፡፡
የሚካሄደው ኹነት በዘርፉ ያሉ ማነቆዎችን ማሳየት ያስችላልም ተብሏል፡፡ የቱሪዝም አውደ ርእይው የአዲስ አበባን የዲፕሎማሲ ማዕከልነትን ከግምት ውስጥ ያስገባ መኾኑም ተመላክቷል፡፡ ኢትዮጵያ ያላትን ትክክለኛና ድንቅ ማንነቷን በአግባቡ ለማስተዋወቅ የሚያስችላት መኾኑንም ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ ያልታየውን ገጽታዋን ለመላው ዓለም ማስተዋወቅ የምትችልበት ኹነት እንደሚኾንም ገልጸዋል፡፡ ቱሪዝም ከሀገር ገጽታ ግንባታ ጋር በቀጥታ ግንኙነት አለው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ የመገናኛ ብዙኃን የኢትዮጵያን ትክክለኛ ማንነት ማሳየት በሚያስችል መልኩ የሚሠሩበት አማራጭ መመቻቸቱንም ተናግረዋል፡፡
መገናኛ ብዙኃን ኢትዮጵያ በፈተና ወቅት በነበረችበት ጊዜ እውነታውን ለዓለም በማስታዋወቅ ታላቅ አስተዋጽዖ እንደነበራቸው ያስታወሱት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ በቱሪዝም አውደ ርእይውም ትክክለኛ የኢትዮጵያን መልክ ለዓለም እንዲያስተዋውቁ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ዘጋቢ፦ ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!