ዓለም አቀፍ ተቋማት ቃል የሚገቡትን ወደ ተግባር እንዲቀይሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መጠየቃቸውን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገለጸ።

32

ባሕር ዳር: ሰኔ 17/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ዓለም አቀፍ ተቋማት ቃል የሚገቡትን ወደ ተግባር መቀየር እንደሚገባቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ( ዶ.ር) መጠየቃቸውን የመንግስት ኮምዩንኬሽን አገልግሎት ዛሬ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡

የመንግሥት ኮምዩንኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ በሰጡት መግለጫ በፈረንሳይ በተካሄው ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ጉባኤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ተገኝተው ንግግር ማድጋቸውን አስታውሰዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የታደጊ ሀገራት የኢኮኖሚ ጫና እና የእዳ አከፋፋል ስርዓት ላይ መልእክት ማስተላለፋቸውንም ተናግረዋል፡፡ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት የአሠራር ማሻሻያ ማድረግ እንደሚገባቸው መናገራቸውንም ሚኒስትር ዴኤታዋ ገልጸዋል፡፡

ዓለም አቀፍ ተቋማት ቃል የሚገቡትን ወደ ተግባር መቀየር እንደሚገባቸውም ጠይቀዋል ነው ያሉት፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል በዓለም አቀፍ ደረጃ ቃል የተገቡ ጉዳዮች በአፋጣኝ መፈጽም እንደሚገባቸውም አንስተዋል ብለዋል፡፡

በተመድ የተያዘው ቀጣይነት ያለው የልማት ግቦች ለታዳጊ ሀገራት ቃል የተገቡት ወደ ተግባር እንዲገቡም ጠይቀዋል ነው ያሉት፡፡ የልማት ካፒታልን ለታዳጊ ሀገራት በሚገባው ልክ ማድረስ እንደሚገባ መግለጻቸውም ታውቋል፡፡

ለታደጊ ሀገራት ጠቃሚ የኾነው የልማት ፋይናንስ ሊሠራበት ይባልም ብለዋል ነው የተባለው፡፡ ዓለም አቀፍ ተቋማት የአረንጓዴ ልማትን ትኩረት እንዲሰጡም ጠይቀዋል ተብሏል፡፡ የአረንጓዴ ልማትን የእድገታቸው ምንጭ ላደረጉ ሀገራት ድጋፍ እንዲደረግም መልእክት አስተላልፈዋል፡፡

በኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ ልዩ ትኩረት የተሰጠው እና ኢትዮጵያ ከራሷ አልፋ ለሌሎች ዓለም ሀገራት ያቀረበችው ስጦታ መኾኑን አንስተዋልም ነው የተባለው፡፡

በኢትዮጵያ የሚተከሉ ችግኞችን ወደ 50 ቢሊዮን ከፍ ለማድረግ እየተሠራ እንደሆነና ዓለም አቀፍ ተቋማት ለዚህ ተግባር ድጋፍ እንዲያደርጉም ጠይቀዋል ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን ለመቻል እያደረገች ያለችውን ትኩረት ማንሳታቸውም ተመላክቷል፡፡ ኢትዮጵያ ምርታማነትን ለማሳደግ እየሠራች መኾኗን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምርታማነትን ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ድጋፍ እንዲያደርጉ በመድረኩ ጠይቀዋልም፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና ሉዑካቸው በፈረንሳይ ቆታቸው ከተለያዩ ሀገራት እና ከዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት መሪዎች ጋርም ምክክር አድርገዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleዓለም አቀፋዊና ቀጣናዊ ኹኔታን በመገንዘብ ብሔራዊ ጥቅም ማስጠበቅ የሚያስችል የዲፕሎማሲ አቅጣጫ መከተል እንደሚያስፈልግ አቶ ደመቀ መኮንን ገለጹ።
Next articleከ232 ሺህ በላይ ሜትሪክ ቶን የአፈር ማዳበሪያ ወደ አማራ ክልል መላኩን የመንግሥት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት ገለጸ።