
ባሕር ዳር: ሰኔ 17/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ዓለም አቀፋዊና ቀጣናዊ ሁኔታን በመገንዘብ ብሔራዊ ጥቅም ማስጠበቅ የሚያስችል የዲፕሎማሲ አቅጣጫ መከተል ያስፈልጋል ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ገልጸዋል።
በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ የምክክር መድረክ በማካሄድ ላይ ነው።
በምክክር መድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን፣ “ዓለም አቀፋዊና ቀጠናዊ ሁኔታን በመገንዘብ ብሄራዊ ጥቅም ማስጠበቅ የሚያስችል የዲፕሎማሲ አቅጣጫ መከተል ያስፈልጋል” ብለዋል።
መድረኩ የዲፕሎማሲ ስራዎች ላይ ምክክር ለማድረግ የሚያስችል ነው፤ ይህ የመጀመሪያው የምክክር መድረክ ቢሆንም፣ በቀጣይ በየአመቱ የሚካሄድ ይሆናል ሲሉም አቶ ደመቀ ተናግረዋል።
የምክክር መድረኩ አሁን ያለውን አለም አቀፋዊና ቀጠናዊ ሁኔታን ከመቼውም በላይ በመገንዘብ የሀገራችንን ብሄራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ፣ ወዳጅ ለማብዛትና በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ ተደማጭነት ለማብዛት ይጠቅማል ሲሉም ገልጸዋል።
ያለፉት ሁለትና ሶስት አመታት በዲፕሎማሲው ዘርፍ እጅግ ጫና የበዛበት ነበር ያሉት አቶ ደመቀ፤ በዲፕሎማቶችና በህዝቡ ታታሪነት መስመር ሳንለቅ ቆይተናል ብለዋል። ይሁን እንጅ አሁንም የተለያዩ ጫናዎች መኖራቸውን ጠቁመዋል።
በምክክሩ ላይ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት፣ አምባሳደሮች፣ አንጋፋ ዲፕሎማቶች፣ ተመራማሪዎችና ምሁራን መገኘታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!