
ፍኖተ ሰላም: ሰኔ 17/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የዞኑ ገቢዎች መምሪያ ኀላፊ ወይዘሮ ታዛሽወርቅ መስፍን ለአሚኮ እንደተናገሩት በበጀት ዓመቱ ከመደበኛና ከከተማ አገልግሎት 2 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ ነበር። እስካሁን ድረስ ከ1 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በላይ በመሰብሰብ የእቅዱን 83 በመቶ መፈጸም ተችሏል ብለዋል።
እቅዱን ለማሳካትና አስፈላጊውን ገቢ ለመሰብሰብም በቀሪ የገቢ መሰብሰቢያ ቀናት ርብርብ ይደረጋል ብለዋል።
ገቢ አሰባሰቡም ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር እድገት ማሳየቱን ያስታወቁት ኀላፊዋ የማኀበረሰቡ ግብር የመክፈል ባሕል ማደግ፣ ፍትሐዊ የግብር አጣጣልን ማስፈን መቻሉ እና ከባለድርሻ አካላት ጋር ቅንጅታዊ አሠራር እንዲዳብር መደረጉ ምክንያት ናቸው ብለዋል።
የቀን ገቢን አለማሳወቅ፣ ደረሰኝ አለመቁረጥ፣ የአድራሻ ለውጥ ማድረግና መሰል ችግሮች በግብር ከፋዩ የሚስተዋሉ መኾናቸውን ያነሱት ወይዘሮ ታዛሽወር የባለሙያ ድጋፍና ክትትል በማድረግ አስፈላጊውን ገቢ አሟጦ ለመሰብሰብ ርብርብ ይደረጋል ብለዋል።
እስካሁን በተሰበሰበው ገቢም የማኀበረሰቡን ኢኮሚያዊ ፣ማኀበራዊና ሌሎች የልማት ፍላጎቶች ለማሟላት እየተሰራ መኾኑንም አመላክተዋል።
ዘጋቢ፦ ዘመኑ ይርጋ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!